temple-of-yeha

ፅላት አቅፎ የሚኖር ህዝብ ኣትበድል የቀጠለ

“ፅላት አቅፎ የሚኖር ህዝብ አትበድል።” #Yemane_Nagesh

ከባለፈው የቀጠለ………

ገዳም መስቀለ ክርስቶስ ገለው ትግራይ ስሓርቲ ሳምረ

 

ገዳመ መስቀለ ክርስቶስ ገለው………… በትግራይ ክልል ስሓርቲ ሳምረ ወረዳ(የኢትዮጵያ የቅዱሳን ታሪክ በሚል መፅሐፍ በስለዋ ወረዳ ይለዋል) ከመቐለ 40 ኪሎ ሜትር ወደ ደቡብ አቅጣጫ(ወደ ሳምረ ከተማ በሚወስድ መንግድ) እንደ ተጓዙ ከዓዲ ዓውሶ የገጠር ከተማ አልፈው ዓዲ ግባ የምትባል ትንሽየ መንደር ሲደርሱ ወደ ቀኝ ታጥፈው 30 ደቂቆች በእግር ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ተጉዘው  የሚገኝ  ጥንታዊና የተቀደሰ  ስፍራ ነው። ከገዳምነቱም አልፎ ለብዙ በሽተኞችና ስጋ ደዌ ለፅናባቸው ወገኖች የፈውስ በር ሆኖ እያገለገለ የኖረና ያለ፣ የፈጣሪ ፀጋ የበዛበት ቅዱስ መካን ነው። ይህ ገዳም በ515ዓ/ም በቅዱስ ኣባታችን ኣቡነ መሰቀለ ክርስቶስ  ተመስርቶ በየ መዋእሉ በአፅራረ ቤተክርስትያን ሲጋይ፣ ሲወድቅና ሲነሳ የቆየና በ15 ክ/ዘ መጀመርያ እንደገና ወደ ነበረበት ገዳምነቱ የመጣ ገዳም ነው ገዳመ መስቀለ ክርስቶስ ገለው።

ገዳሙ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ዶግማና ቀኖና የሚመራ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ገዳማትና አድባራት ለዬት ያለ ፀጋና የገዳም ስነ ስርዓት ያለው በጣም እፁብ ድንቅ ገዳም ነው። ይሄም ለአባታችን አቡነ መስቀለ ክርስቶስ ከፈጣርያቸው የተሰጣቸው ፀጋና ቃልኪዳን መሰረት ከአምልኮ እስከ ፀበል ጥምቀትና ፈውስ ፣ሳይሸራረፍ በምእመኑ ስለሚተገበር ነው።  የገዳሙ ህግጋት ሲበዛ በጣም ጥብቅ ናቸው። እንቅልፍ ከቶ ኣይታወቅም። የመኝታ ሰዓት ከምሽቱ 3:00- 5:30 ብቻ ነው። ከ24 ስዓት ሙሉ 2:30 ብቻ ሸለብ ይላሉ ማለት ነው። ጤነኛ ይቅርና በሽተኞችም ታዝለውም ይሁን በቃሬዛ ተሸክመው አልያም በሰንሰለት ታስረው ወደ ፀሎትና ምህላ መሄድ የግድ ይላል።

በዚህ ገዳም ውስጥ ብዙ የእግዚአቢሒር ፀጋ የበዛላቸው አባቶች ከመኖራቸው አንፃር ከተለያዩ የኢትዮጵያ መአዝኖች የመጡ ወገኖች ማየት የተለመደ ነው። እኔ በበኩሌ አማራዎች ግማሽ ያክል ፣ የተወሰኑ ኦሮሞዎች፣ሲዳማዎች፣ አማሮዎች(ዲላ አካባቢ ከሚገኝ ብሄረሰብ) ፣ ጉራጌዎች፣ ከድሬዳዋና ሃረር የመጡ ብቻ ከመላው የሃገራችን ክፍል የተሰበሰበ ህዝብ አይቻለሁ። መግባብያ ቋንቋም አማርኛ ነው።

በዚህ ገዳም ውስጥ መግብያው ላይ ጫት፣ ሲጋራ፣ ሽንኩርት፣ ዜይት፣ ቡና፣ ሻይና አነቃቂ ንጥረ ነገሮች ይዞ መግባት በፈጣሪ ስም የተከለከለ ነው ይላል።ተንቀሳቃሽና ደረቅ ምስል መቀረፅም ሆነ ማንሳት ፍፁም ክልክል ነው። በተለይ ደግሞ በህክምና የሚሰጡ የዕድሜ ልክ መድሃኒቶች ይዞ መግባት ኣይፈቀድም። የሚገርመው መድሃኒት ካልዋጠ ለደቂቃ መቆየት የማችል ሁሉ መድሃኒቱን ሰገራቤት ከቶ በጤንነት እየተጓዘ ስያዩ፣ እውነት ዘመናዊው የህክምና ሳይንስ አንድ ያላስተዋለውና የሳተው የእውቀት ኣድማስ እንዳለ ያመላክታል። አንድ ከሃዋሳ -ጪሮ ኣካባቢ የመጣ ሰው ሲነግረኝ “ከፍተኛ የልብ ድካም አለብኝ ። መድሃኒት ካልዋጥኩ 20ሜትርም መጓዝ ይከብደኝ ነበር። እዚ ከመጣሁ 15ቀን ሆኖኛል። እንደምታየኝ ከናንተጋር ድንጋይ ተሸክሜ ዳገት እየወጣሁ ነው።” ሲለኝ ደንቆኛል።

“የማይሰራ አያብላ” የሚል የቤተ ክርስትያኒቱና የመፀሐፍ ቅዱስ የተቀደሰ ሃይለቃል ሳይሸራረፍ ይተገበራል። በገዳመ መስቀለ ክርስቶስ ሽራፊ ሴኮንድ አለአግባብ አትባክንም። ሁሉም በስራ ተጠምዶ አልያም በፀሎትና ስግደት ሲለፋና ፈጣሪውን ሲያመልክ ይውላል። በገዳሙ ውስጥ ቁጥራቸው የማይታወቅ ወጣትያን፣ መናንያን፣ መነኮሳትና ባህታውያን ይገኛሉ። ከነዚህ ውስጥ ሱባኤ ያልገብቱ ፣ የእርሻ መሳርያዎቻቸው ራሳቸው አሹለው፣ በሬ ጠምዶ ማረስ፣ ድንጋይ መፍለጥ፣ መሸከም ፣አሸዋ ማመላለስ መቆፈር ፣ ቤት መገንባት፥ አርማታ መሙላት፣ የታመሙ በሽተኞች አዝሎ ማመላለስ ፣ እንጀራ መጋገር፣ ጠላ መጥመቅ፣ ሰራተኞች ማሰናገድ፣ እግር ማጠብ ወዘተረፈ የማይሰሩት ስራ የለም። ሲበዛ “ቢዚ” ናቸው። ጠበል የሚታጠብ ሰውም ያንኑ የማድረግ ግዴታ አለበት። ካለበለዛ ሴጣን ያሸንፈዋልና ነው።

ገዳሙ ሲገቡ ስጋዊ ፍላጎት በራሱ ግዜ እልም ብሎ የጠፋለዎታል። ገዳማዊ ህይወት ይመችዎታል። ለካ ሰው ስራ ሲፈታ ነው ደስተኝንቱም የሚጠፋበት! አልያም ከፈጣሪው መጣላት የሚጀምረው። ደስ የሚል ህይወት በገዳመ መስቀለ ክርስቶስ!!! የደነደነው ልብዎትን መፍረስና ለእግዜአቢሔር መገዛት የሚጀምረው፣ ገና የገዳሙ በር ሲረግጡ ግዜ ነው። እቃዎትና ጓዝዎት ከበር ተቀብለው የሚያስቀምጡ ለበረከት ብለው የተመደቡ ምድብተኛ አሉ። ልክ እንደ ገቡ እግርዎትን በውሃ ያጥቡዋቸዋል። አጥበው እንደ ጨረሱ አጣቢዋ ወይም አጣቢው እግርዎትን ይሳለምና(ይስምና) ልዑኩን ይጨርሳል/ትጨርሳለች። ያኔ የደነደነ ልብዎትን እንደ እምቧይ ካብ መፍረስ ይጀምራል። ትህትና በትህትና መማር ይጀምራሉ።ቀጥለውም እንደ እንግዳነትዎ የገዳሙ መመርያዎች በዘመናዊ ህትመት ከታተመው መፅሐፍ በጥብቅ ይነበብለዎትና ወረፋ ሳይጠብቁ ደረጃ በደረጃ ፀበሎችና ልዩ ልዩ ግልጋሎቶች እንዲያገኙ ይደረጋል።

ፅላት አቅፎ የሚኖር ህዝብ አትበድል…………ተናጋሪው የማነ ናግሽ ነው።

“““““““““““““““““““““““““

ሃይማኖት ፖለቲሳይዝ ማድረግ ኩፍኛ መጥፎ መሆኑን እረዳለሁ። ግን ደግሞ መገለፅ ያለበት ሃቅ ሲገኝ እሬት እሬት እየመረረም ቢሆን በግድ ይነሳል። ፖለቲሳይዝም ይደረጋል። ዋናው ነገር ኣጀንዳው ህዝብ ለማጥፋት ነው ወይስ ህዝብን ካላስፈላጊ ግጭትና ቁርቁስ ለማዳን የሚል ነው። ገዳመ መስቀለ ክርስቶስ ዕረፍትና እንቅልፍ የሉም ብያችዋለሁ። ከሌሊቱ 5:30 እስከ ቀኑ 7:00 ስዓት ምህላ፣ ፀበል መጠመቅ፣ ርጭት፣ ፀበል መጠጣት ፣ በስራ ምድብተኛም እላይ የገለፅኳቸው ልዩ ልዩ ስራዎች ያከናውናል። ዘሮ ወደ ምኝታ መግባት የተከለከለ ነው።ከቀኑ 7:00-9:00 ርጭት ተረጭቶ ፀበል በባዶ ሆድ ይጠጣል። 9:00ስዓት  እህል ወሃ የሚባልበት አጭር ክፍለ ግዜ አለ። እህል ውሃ ከቀማመሱ ደወል ይደወልና ወደ ፀሎት። እስክ 11:00 ፀሎትና ምህላ ይደረጋል። ከ11:00 -12:00 ባለው ግዜ ዝክርና ትምህርት ይደረጋል። 12:00- የምሽቱ 1:00 የእራት ክፍለ ግዜ ሆኖ እስከ ሁለት ስዓት ሰው የሚፀዳዳዱበት ክፍለ ግዜ ነው። የፀሎት ደወል ሁለት ስዓት ይደወልና ፣ምዕመኑ በፍጥነት በሩን ሳይዘጋ ወደ አውደ ምህረት ለፀሎት ይተማል። ፀሎት እስከ ሦስት ስዓት ይደረጋል። ከሦስት ስዓት በኋላ የእንቅልፍ ስዓት ነው። መልሶም እንደተለመደው የሌሊቱ 5:30 ደወል ይደወላል። ሁሉም ምእመን በሩን ሳይዘጋ ወደ አውደ ምህረት ይገባል።

ህጉና ስነ ስርዓቱ ጥብቅ ከመሆኑም የተነሳ የሴቶችና የወንዶች የየቀኑ ተቆጣጣሪና መዝገብ ጠሪ አለ። የቀሩ እንደሆነ ከባድ ቅጣት ይጣልበዎታል። 20 ድንጋይ ወይም 10 መዳበርያ አሽዋ እንደየ አቅምዎ እየታዬ ቅጣት ይጣልቦታል። ማደርያ ሰፈርም በተረኞ ተባቂዎች ይጠበቃል። መርፌም ቢሆን መጥፋት አትችልም። ሁለመና የሰውሃይል አየያዝና አስተዳደር ሲበዛ ዘመናዊ ነው። ገዳሙ ለጤንነትዎና መንፈሳዊ ህይወትዎ ብቻ አይደለም የሚያስተካክልለዎት። የግዜ አጠቃቀማችንም ጭምር ትልቅ ማሰልጠኛ ነው ማለት ይቻላል። እቤቱ የራሱ ካልሲ አጥቦ የማያውቅ ቅምጥል ሁሉ የሰው እግር አጥቦ ሲስም፣ ድንጋይና አሸዋ እያጋዘ ሲያዩ እውነት ያቦታ ቅዱስ መሆኑን ይረዳሉ። የሚገርመው የምግቡ ነገር ነው። ሲፈጉ አድረውና ውለው የሚያገኙት ምግብ ሁሉም ይጥማል። ካለ ዘይትና ሽንኩርት የተሰራ ምግብ በልተው መጥገብ ነውር ነው። እየጣፈጥዎት ይተውታል እንጂ። ሌላ ይቅርና በጨው ብቻ የተሰራ ቦሶም ከጥብስ በላይ ይጥማል። የበሉት ምግብ ወዴት እንደሚገባም አይታወቅም። እንደ ግመል  በሦስተኛው ቀን አንድ ፍሬ ብቻ ከጣሉ ነው። በሽታዎት የት እንደ ገባ አይታወቅም። ያገኙትን በልተው  በደስታ መዋል ማደር! ደስ ሲል!

ገዳሙ ትግራይ ክልል ነው ያለው። ዙርያውም በገበሬ ቤቶች የተከበበና ዕለታዊ ገዳሙ የሚፈልጋቸው ነገሮች በገበሬዎቹ የሚሟላለት ነው።እናቶችም አባቶችም አማርኛ ምን እንደሆነች የማያውቁ።ግን ደግሞ መግባብያ ቋንቋ አማርኛ ነው። የሚገርመው መነኮሳቱም አማርኛ አጥርተው መናገር አይችሉም። መግባብያ ቋንቋ አማርኛ በመሆኑም ግማሽ ትግርኛ ግማሽ አማርኛ ሚስቶ አማርኛ ተጠቅመው ምእመኑ ሲያስተምሩ ይውላሉ። አብዘሃኛው ህዝብ በደመነፍስ ያዳምጣል። ችግሩ ምህላ ላይ ነው። ምህላ የሚመሩ መነኩሴዎች ሁሉም መዝሙራቸው በትግርኛ ነው። ከመላ ሃገሪቱ የተሰባሰበ ፍጥረት በትግርኛ ሲዘምር ማየት እንዴት ደስ ይላል። ተሎ ይለምደዋል። ለካ ሰው በገዛ ፍቃዱ ሲሰባሰብ ቋንቋና ጎሳ ኣይገድበውም። የምህላ መዝሙሮችና ዜማዎች ሲዘመሩ የራሱ ልዩ እንቅስቃሴና የአምልኮ ስነስርዓት አለው። በየዝሩ እግዚኦ……… አለ።  እግዚኦ መሃረነ ክርስቶስ፣ በእንተ እግዚእትነ ማርያም መሃረነ ክርስቶስ፣  በእንተ ኩሎሙ መላእክት…………………በእንተ ኩሉ ዓለም ፍጥረት የሚሉት ከሚደርሱት ምልጃዎችና ልመናዎች ይገኝባቸዋል።

ከሁሉም ብሄር ብሄረሰብ በአንድ መአድ ያለ ምንም ልዩነትና ተፃብኦ መገኘት ፣ ተቃቅፎ መዋል ማደር እንዴት ልብ ይነካል። ያኔ በትግራዋይነቴ፣ አማራነቴ፣ ኦሮሞነቴ፣ ሲዳማነቴ፣ ጉራጌነቴ………………ባጠቃላይ በኢትዮጵያውነቴ የኮራሁበት ሳምንት ነበር። ለምን በሉኝ! የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች በትግርኛ እየዘመሩ በአውደ ምህረት ከትግራይ  እናት አባቶቻቸው እየቦርቁ ማየት ፣ ልክ ሴት ልጅ ካማች ቤት(ከጫጉላ ቤት) ስትመለስ ግዜ የምታሳየው ደስታ ያክል ነው። የትግራይ ህዝብ የሁሉም ብሄሮች የእናትነት ሃላፊነት የተሸከመ እስኪመስል ድረስ እንግዶቹን ሲንከባከብና በጥንቃቄ ስይዝ ይታያል። በዚህ ንፁህ ህዝብ መሃል እኔ ብቻ ነበርኩኝ የጠባብነት አባዜ የሚሸነቁጠኝ። ምክንያቱ እንደ ህዝቡ በስራላይ አልውልምና ፣ ፌስቡክ፣ ፓልቶክ፣ ትዊተርና የተለያዩ ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን እየተከታተልኩ ስለምውል፣ ምን በወጣህ ይሆን ያሁሉ ሽርጉድ ፣ያሁሉ መንከባከብ እያልኩ አልፎ አልፎ ከመጣሁበት አላማ ወጥቼ ወደ ስንፍናና ወደ ሃጥያት ረግረግ አመራለሁ።

ምክንያቱም የገበሬው የዋህነት፣ የከተሜው ለጋስነት፣ አጠቃላይ የትግራይ ህዝብ እንግዳ ተቀባይነትና ለወንድም ህዝቦች የሚያሳየው ኣክብሮትና እገዛ ሳይ፣ እኔ በPaltalkና Facebook ስለሱ ሲዶለትና ሲሸለል የሚውለው የጉድ ጉድ ስለማውቅ በዛምክንያትም ከሚዛናዊ ኣስተሳሰብ ወደ ቆጠኛና ቂም በቀል ቀስ በቀስ በመዝቀጤ ምክንያት ፣ አዬ! በሰማህማ ንሮ እላለሁኝ። ግን የኔ ስንፍና ለህዝቡ ትርጉም የለውምና አንዴ የእግዚኣቢሔር አማኝ በመሆኑ ለወዳጁ ይቅር ለጠላቶቹም ፈጣሪ እንዲምርለት 21:00 ስዓት ሙሉ ፈጣሪውን ሲለምንና ሲማልድ ውሎ ያድራል። ያህዝብ የእግዚኣቢሔር ህዝብ ነው። ከሰማይ እንጂ ከመሬት ጠብቆ አያውቅም። እኔ ሰምቼው ያናደደኛና ወደ ዘረኛ የቀየረኝ የትምክህተኞች የጥፋት ስብከት ለዚህ ህዝብ ምኑም አይደለም። ይልቁንም “በእንተ ኩሉ ዓለም ፍጥረት” እያለ አፈር ሲለብስና ስያለቅስ ያድራል። ስለጠላቶችም ጭምር ማለት ነው። ሞትና እልቂት ለሚደግሱለትም ጭምር ማለት ነው። ካንሰርና ነቀርሳ ነህ ለሚሉትም ጭምር ነው። ቅማላምና ለማኝ ብለው ባደባባይ ለሚሰድቡትና ለሚያዋርዱት ጭምር ነው።

ከምህላ መዝሙሮች የተወሰኑቱ: –

“ኣቲ ማርያም ወይኖ ማርያም ሃና

ኣብ ኢዮሩሳሌም ሰባስብና

ኣቲ ማርያም ወይኖ ማርያም ሃና

ውልድን ወላድን ሓዋውስና ” የሚሉ ይገኙበታል። ትርጉሙም፣

ኣንቺ ማርያም ጠይም ማርያም ሃና

በኢዮርሳሌም ውስጥ ሰባስቢን ፣ ኣባትና ልጅ ኣስታርቂልን እንሰማለት ነው።ይዘቱ ሲመረመር ኣንድም፡ሳታስቀሪ በሰማያዊቷ ኢዮርሳሌም ሁላችንም አስገቢን ማለት ነው። በዚህ ቦታ ጠላት የሚሉት የለም። ሁሉም የአዳም ዘር እዲማር ከመማለድ ውጪ። እኔም እንደ ምእመን በሚቀርቡት የምልጃ መዝሙሮ ከጥልቀታቸው አኳያ ስመዝናቸው ህዝቡ የተከተለው መንገድ ልክ እንደ ሆነና እኔ የደረስኩበት የኣረዳድና የግንዛቤ ደረጃ ዜሮ ያደርግብኛል። በመሆኑም ዓለማዊ እውቀቱ ፉርሽ ይሆንና ህዝቡን መምሰል ግድ ይለሃል።

በገዳሙ ውስጥ ያመከረኛ ፖለቲካ Facebook ላይ የለመድኩትን ለግንዛቤ ያክል ከሌላ ክልል ከመጡ ወንድሞች ስለ ትግራይ ህዝብ ያላቸው አመለካከት እየከበደኝም ቢሆን እጠይቃቸው ነበር። አብዛኞቹ በገዳም ውስጥ ስለዓለማዊ ነገሮች ማዋራት ደስተኛ ባይሆኑም ፣ የህዝቡ ሁለመና የዋህነትና ታታሪነት ሳያስገርማቸው አልቀረም። ግን ደግሞ በዓንድ ነገር ይጠራጠራሉ። ትግራይ ውስጥ ያለ ህዝብና ከትግራይ ክልል ውጭ ያለ የትግራይ ተወላጅ አንድ ናቸው ወይ የሚል ጥያቄ ያነሳሉ። እኔም ጥርጣርያቸው ጥርጣሬ ውስጥ ከትቶኛል። ለምን ቢሉ በተለያየ ክልል የሚኖር ትግራዋይ በስግብግብነት፣ ሌብነት፣ ሙስና፣ አማገነንነት፣ አጭበርባሪነት ፣ ወገንተኛና ጎጠኛ አካሄድ የሚንፀባረቅበት ከሆነ፣ እውነት ነው የትግራይ ህዝብ ታማኝነቱ፣ ለሰው አክባሪነቱ፣ የዋህነቱ ፣ ታጋሽነቱ፣ ፈጣሪ አማኝነቱ ወዘተ በጥቂት ስግብግብ ልጆቹ ቁማር ተበልቷል ማለት ነው።

ከአንድ የኦሮሞ ተወላጅ ዶክተር፣ በሽተኛ ተሸክመን የ40 ደቂቃ ጉዞ ተጉዘን ነበር። መንገድ ላይ ገበሬዎች በሬዎቻቸው ጭምር ኣቁመው በሽተኛው ሲሸከሙና ሲያግዙን ተመልክቷል። መንገድ ላይ ያገኘናቸውም ለተወሰነ ርቀት ተመልሰው ኣግዘውን ሲመለሱ አስተውለዋል። ስንመለስ እያወራንና በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ስንነጋገር ነበር። ልጁ እንዲህ ይላል” እኔ የትግራይ ህዝብ ምን ዓይነት ህዝብ መሆኑን ይገርመኛል። በሌሎች ክልሎች የማታየው የብዙ ጥሩ እሴቶች ባለቤት ነው። ሌላ ክልል ብትሄድ ለ40ና 50 ደቂቃዎች ሰው በነፃ ተሸክሞ መተባበር ይቅርና ፣ የቆመ መኪና ግፋልኝ ብትለው ኣይገፋልህም።” ግን ለምንድን ይሆን በፖለቲከኞችና በሌሎች ብሄሮች ልሂቆች ጥርስ የሚገባው ብዬ ጠየቅኩት። ፈራ ተባ እያለ “እላይ   ባሉ ሰበስልጣንና ስግብግብ ነጋዴዎች ይመስለኛል። ” ይላል። አዎ! ችግሩ ይሄ ነው። የትግራይ ህዝብና በስሙ የተመሰረቱ ድርጅቶችና ከኣብራኩ የወጡ ስግብግብ ባለሃብቶች ለየቅል ናቸው። ዘረኛ አመለካከት ያላቸው ወገኖች ፣ በነሱ የተታለሉ የዋህ ዜጎች መለዬት ያቃታቸው ይሄንኑ ነው። የትግራይ ህዝብ፣ ወያነና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ሶስት የተለያየ ይዘት ያላቸው የተለያዩ ነገሮች።

የትግራይ ህዝብ ከ3000 ዓመት በላይ የኖረና ያለ ህዝብ ነው። ከ40 ዓመት በፊት የተፈጠረ ድርጅት ልደትህ አከብርልሃለሁ ብሎት የካቲት 11 ሲያከብር የድርጅቱ ድፍረትና አላዋቂነት ያሳያል እንጂ የህዝቡን ጥንታዊነትና ታሪካዊነት አይቀንሰውም። በኢትዮጵያ ታሪክ ለዘመናት ለኢትዮጵያ አንድነት ሲል ቀይ ደሙን የገበረ ህዝብና ለኢትዮጵያ ብሎም፡ለአፍሪካ መሰረትነቱ ያረጋገጠ ህዝብ እንጂ። መሰረት በመሆኑም ዳር ድንበር በአጥንቱ ተከላከለ እንጂ የበላይነት ስሜት ላፍታም ቢሆን አሳይቶ አያውቅም። መለያው የእግዚአቢሔር እምነት ነው። መፈክሩም እኩልነት!!! ስለዚ ያህዝብ በየዘመኑ በሚነሱ ዘረኞችና ትምክህተኞች ጦር ለምን ይወጋል ነው። ለምን ተለይቶ ኢላማ ይደረጋል ነው። ለምን ተልይቶ የክሃዲነት  ካባ ይከናነባል ነው።

ስለ እውነት የቆመ ህዝብ ፣ ስለወዳጆቹ ብቻም ሳይሆን የሞት ድግስ ለሚደግሱለትም ጭምር ምህረት የሚለምን ህዝብ ሴይጣን ካልሆነ የሰው ልጅ እንዴት ኩፉውን ይመኝለታል? Paltalkers, Facebookers, ኣክራርያንና ዘርኣውያን ለቀቅ ኣርጉት። “ደም ከፍሎ ውሃ የተከለከል ህዝብ ነው።” አጥንት ከፍሎ ልማት የተነፈገው ህዝብ ነው። እስከ ኣሁን ቆስቋላ ህይወት የሚመራ ህዝብ ነውና ልቀቁት። የፖለቲካ መናገጃ ኣታድርጉት!!!

ወዲ ገረብ ፃና!!!

You may also like...