leul-mengesha-seyoum

ያልተፃፈው መፅሀፍ

አንድ ወዳጄን ከልኡል ራስ መንገሻ ስዩም ጋር ቀጠሮ እንዳለኝ ስነግረው እንዲህ አለኝ ፡፡ – “ ከልኡል ራስ መንገሻ ስዮም ጋር ስትቀመጥ ቤተ መፅሀፍት እንደገባህ ቁጠረው፡፡ ስለ ስራ – ስለ ታሪክ……. ብዙ እውቀት ታገኛለህ፡፡ – አንብበው፡፡ – ልኡል ራስ መንገሻ ማለት ያልተፃፈ መፅሀፍ ነው፡፡ – የማይሰለች ፤ አንብበህ የማትጠግበው መፅሀፍ!!!………. መፅሀፍ ስለሆነ ነው አንተ የምለው፡፡ – መፅሀፍ አንቱ አይባልምና!!!! – እንደ ሰውማ በስራቸው አንቱታውም ሲያንሳቸው ነው!!!……..”
በቀጠሯችን መሰረት – ሳገኛቸው የመንፈስ እና የአካል ጥንካሬአቸውን አስተዋልኩ፡፡ የሰማንያ ዘጠኝ አመት ጎረምሳ!!!
ጨበጥኳቸው፡፡ – ይገርማል!!!….. “ ልኡል – ራስ!!!……..” ሲባል የጠበቅኩት እንደ የታሸ ማንጎ ሲነኩት “ ትሙክ!!!……” የሚል እጅግ የለሰለሰ እጅ ነበር፡፡ – የልኡል ራስ መንገሻ ግን – በስራ የደደረ ጠንካራ እጅ ነው፡፡
ለሀገራቸው ብዙ – ብዙ የለፉ ፤ ብዙ የደከሙ ግን ብዙም ያልተነገረላቸው – ልኡል ራስ መንገሻ ስዮም፡፡ እየተጨዋወትን – በልኡሉ ውስጥ ቅድመ አያታቸውን አፄ ዮሐንስን አየኋቸው፡፡ – ለሀገራቸው ድንበር መጠበቅ ሲባዝኑ ኖረው – በመጨረሻም ለሀገራቸው ድንበር መከበር መተማ ላይ አንገታቸውን የሰጡ ጀግና ሰማእት፡፡ – አፄ ዮሐንሰ የጀግንነታቸውን ያህል የማይነገርላቸው – ክብር ያልተሰጣቸው – አፄ ዮሐንስ!!! ድንበር ለማስከበር እንደተንከራተቱ ያረፉ – አፅማቸው የት እንዳረፈ እንኳ የማይታወቅ ፤ ለማወቅም የማይፈለግ – የእነቸርችል ፤ የእነዊንጌትን ያህል እንኳ ስማቸው የማይነሳው ንገሰ ነገስት – አፄ ዮሐንስ
ልኡል ራስ መንገሻ ስዮም በሚጥም አንደበታቸው – ታሪካቸውን ኮመኮምኩኝ፡፡ ብዙ ሰርተው እንደ ቅድመአያታቸው ታሪካቸው የተዳፈነ ልኡል፡፡
የትግራይ ህዝብ ፍትህ በመጓደሉ ምክንያት አመፅ አስነስቶ መቐለ ላይ ውግያ አካሂዶ ከግንቦት 29/1935 እስከ ጥቅምት 4/1936 ዓ.ም መቐለ በቀዳማይ ወያነ ሰራዊት ቁጥጥር ስር ቆይታለች፡፡ እነ ራስ አበበ አረጋይ በሰጡት ትእዛዝ ከየመን የተነሱ የእንግሊዝ የጦር ጀቶች ከተማዋን በቦንብ በመደብደብ ከ2500 በላይ ንፁሀን የከተማው ነዋሪዎች ጭምር አልቀው ራስ አበበ እና ሜጀር ጄነራል አበበ ዳምጠው ጦራቸውን ይዘው መቐለ ሲገቡ – ልኡል ራስ መንገሻ “ ቀዳማይ ወያነን አስተባብረሀል!!!…….” ተብለው ታስረው ወደ አዲስ አበባ ተላኩ፡፡
የሞት ፍርድ እንዲፈረድባቸው ብዙ ጥረት ቢደረግም – እድሜያቸው ገና አስራ ሰባት አመት ስለነበረ አፄ ሐይለስላሴ ምህረት አድርገውላቸው – ከአካባቢውም እንዲርቁ በማሰብ ቤሩት ለትምህርት ተላኩ፡፡
ልኡል ራስ መንገሻ ከትግርኛ እና አማርኛ ቋንቋዎች በተጨማሪ ጣልያንኛ፤ እንግሊዘኛ አቀላጥፈው ይናገራሉ፡፡ ኦሮምኛም በትንሹ መስማትና መናገር ይችላሉ፡፡ – በፈረንሳይኛ እና በአረብኛም አይታሙም፡፡
እውቀታቸው ጥልቅ ነው፡፡ – የዚህ ሚስጥሩ ደግሞ መፅሀፍ አንባቢነታቸው እና ስራ ወዳድነታቸው መሆኑን ወዳጆቻቸው ይናገራሉ፡፡ እኔም ከልኡሉ ጋር በነበረኝ ቆይታ ያረጋገጥኩት ይኸው ነው፡፡
በሀገራችን ታሪክ ውስጥ ጉልህ ቦታ ያላቸውን ክስተቶች እየተነተኑ ሲተርኩ በቦታው እና በግዜው ያሉ ያህል ሰሜት እንዲሰማ ያደርጋሉ፡፡ – ወዳጄ – ልኡል ራስ መንገሻ ስዩምን “ ያልተፃፈው መፅሀፍ!!!……..” ብሎ የገለፃቸው ትክክል ነው!!!……. ስል ደመደምኩ፡፡
ልኡል ራስ መንገሻ በሀገራችን በርካታ ተግባራት ላይ አሻራቸውን አሳርፈዋል፡፡ ቤሩት ተምረው ሲመለሱ ስራቸውን የጀመሩት የአምቦ አስተዳዳሪ ሆነው ነው፡፡ (ሲሾሙ “ገዥ!!!…..” ቢባሉም ለስራ የሚታትር ገዥ!!!…….. ስለማላውቅ – ባለችኝ ሚጢጢ እውቀት – “ አስተዳዳሪ!!!….” የሚለውን ቃል ተጠቅሜአለሁ፡፡)
– ወረዳዎችን ከአውራጃው ለማገናኘት ስለሰሯቸው መንገዶች – ህዝቡ የመብራት ሀይል እንዲያገኝ ስለአደረጉት ጥረት አምቦ ትመስክር፡፡
– ከባሌ ጠቅላይ ግዛት ጋር የሚያገናኛት ትልቁ የገናሌ ወንዝ ድልድይ የተሰራላት ፤ አውራጃዎች ከአውራጃዎች ለማገናኘት መንገዶች የተዘረጉላት ፤ ነዋሪዎቿ ፀጉራቸው የሱፍነት ባህሪ ያለው – የተዳቀሉ በጎች እንዲያረቡ እና ለገበያ እንዲያቀርቡ – በባለቤታቸው ልእልት አይዳ ደስታ (የአፄ ሐይለስላሴ የልጅ ልጅ) አማካይነት የሴቶች የባልትና ልማት ማህበር በኢንዱስትሪ ደረጃ ተቋቁሞ ከበጎቹ ፀጉር ምንጣፍ እና ሹራብ አምርቶ ለገበያ እንዲያቀርብ በማድረግ የገበያ ትስስርን የፈጠሩባት ፤ የህዝቧን የውሀ ችግር ለመፍታት ከአለም ባንክ ፈንድ በማፈላለግ የውሀ ጉድጓድ ያስቆፈሩላት አርሲ አፍ ቢኖራት ስለ ልኡል ራስ መንገሻ ስዩም – ክብር ብዙ ትመሰክራለች፡፡
– በቅርቡ 50ኛ አመቷን ያከበረችው ሐዋሳ – ታቦር ተራራ ላይ ድንኳን ደኩነው – እንድትቆረቆር የደከሙላት እና ፕላኗንም ያሰሩላትን ልኡል ራስ መንገሻ ስዩምን – የክብር አባቷን – በክብር ጠርታ ስለክብራቸው መመስከሯ – ወትሮም የምወዳት ሐዋሳን እጅግ አከበርኳት፡፡
የዛሬ 126 አመት ከደርቡሾች ጋር ሲፋለሙ ወድቀው አንገታቸውን የሰጡላትን – አፄ ዮሐንስን ሁሌም የምታስባቸው – የምትዘክራቸውን የዮሐንስ መተማን አሰብኳት፡፡ – አክባሪ ክቡር ነውና ፤ የዮሐንስ መተማ ስለክብርሽ እመሰክራለሁ፡፡ በየሄድኩበት ላወድስሽ ዛሬም በመሀላ – ቃል እገባለሁ፡፡
ዮሐንስን!!!!
የዮሐንስ አምላክ ይጠብቅልኝ!!!……… ክፉ አይንካብኝ!!!
ለመሆኑ – ልኡል ራስ መንገሻ ለመጀመሪያ ግዜ ከእንጨት ያሰሯት 12 ሰው የመያዝ አቅም ያላት የሐዋሳ ሐይቅ ጀልባ በቅርስነት ሙዝየም ገብታ ይሆን?
ከ1949 -1953 ዓ.ም ታሕሳስ ወር ድረስ በስራና መገናኛ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ልኡል ራስ መንገሻ በብዙ ውጣ – ውረዶች ውስጥ አልፈው የአስመራው የአፄ ዮሐንስ 4ኛ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን እና የአዲስ አበባውን ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያን አሰርተዋል፡፡
በወርሀ ሚያዝያ 70ኛ የምስረታ አመቱን የሚያከብረው – የሀገራችን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካውያን ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ገና በእንጭጭነቱ – በአስራ አምስት አመቱ የፕሮፔለር ሞተር ያላቸውን ዳሽ – ተብለው የሚጠሩትን አውሮፕላኖች ይዞ በአለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠል እንደማይችል እና ለመሞት እያጣጣረ እንደሆነ የተረዱት – የቦርዱ ሊቀመንበር የነበሩት – የስራና መገናኛ ሚኒስትሩ የዛን ግዜው ደጃዝማች መንገሻ ስዩም ፤ ከሀገራችን ከፍታ እና አየር ፀባይ ጋር ተስማሚ የሆነው ቦይንግ 720 – የጄት ሞተር ያለው አውሮፕላን እንዲጠና አድርገው – ለቦርዱ ካቀረቡ እና እንዲገዛ ካፀደቁ በኋላ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር በነበሩት አቶ አክሊሉ ሐብተወልድ የሚመራው የሚኒስትሮች ምክርቤት “ ገንዘብ የለንም!!!……” በሚል ምክንያት እቅዳቸውን ውድቅ አደረገባቸው፡፡ ለአፄ ሐይለስላሴ ይግባኛቸውን ያቀረቡት ልኡል ራስ መንገሻም አየር መንገዱ ላይ ያንዣበበውን የመክሰም አደጋን በሚገባ አስረድተው ለአይሮፕላኖቹ ግዢ የሚያስፈልገውን የ45,000,000 (አርባ አምስት ሚሊዮን) የአሜሪካን ዶላር ብድር ራሳቸው ሊያፈላልጉ የመንግስት ውክልና እንዲሰጣቸው ጠየቁ፡፡
የሚኒስትሮች ምክር-ቤትን ውሳኔ “ ይግባኝ!!!…………..” ብሎ አፄ ሐይለስላሴ ፊት የቀረበ ሚኒስትር አጋጥሟቸው ስለማያውቅ መገረማቸውን የገለፁት ንጉሱ ፤ጠቅላይ ሚኒስቴሩን አስጠርተው ካነጋገሩ በኋላ ልኡል ራስ መንገሻ ፈንድ ለማፈላለግ የመንግስት ውክልና ተሰጣቸው፡፡
ከብዙ ጥረቶችን አድርገው – ለአሜሪካ መንግስት ያቀረቡት የብድር ጥያቄ ተቀባይነት አገኘ፡፡
“……..ገንዘቡ ሲፈቀድ በደስታ እግሬ ተንቀጠቀጠ!!!…..” ይላሉ የዛን ግዜው የስራና መገናኛ ሚኒስትር – ደጃዝማች መንገሻ ስዩም፡፡
የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊው ካፒቴን አለማየሁን ያካተተ ቡድን ለበረራ እና ለጥገና ባለሙያነት ስልጠና ወደ አሜሪካ እንዲላክም አደረጉ፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድን ከመፍረስ ታደጉ፡፡
የልኡል ራስ መንገሻ ስዩም ስራ ለመዘርዘር መፅሀፍ – መፅሀፍት አይበቁም፡፡ ከጥቂቶቹ ግን በጥቂቱ ልጥቀስ
– የአሰብ የነዳጅ ማጣሪያ ብዙ የደከሙበት የፕሮጄክታቸው ውጤት ነው፡፡
– የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አዳራሽ የ3 አመታት የግንባታ እቅድ 24 ሰአት በመስራት በአንድ አመት እውን እንዲሆን አድርገዋል፡፡
– “ ባህር ዳር ተለዋጭ የመናገሻ ከተማ ትሆናለች!!!……” የሚል እቅድ ስለነበራቸው አብደርምስታድ በተባለ የጀርመን ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች ፕላን እንዲሰራላት አድርገዋል፡፡ ዛሬ – የተመልካች አድናቆት የሚቸራት ባህርዳር – ባለ ውለታዋ ናቸው፡፡ – ልኡል ራስ መንገሻ ስዩም
– የኢትዮ – ጅቡቲ የምድር ባቡር 75ኛ አመቱን ሲያከብር – ልኡል ራስ መንገሻ ለፈረንሳይ መንግስት ሀሳብ በማቅረብ እና የማሳመን ስራ በመስራት ሙሉ በሙሉ በፈረንሳዮች ቁጥጥር ስር የነበረው የምድር ባቡር ድርጅት – የዳይሬክተርነት ስልጣን በፈረቃ እንዲሆን ፤ ቴክኒሻኖችም ኢትዮጵያውያን እንዲሆኑ እና ነፃ ድርጅት እንዲሆን አደረጉ፡፡ ኢትዮጵያ የጅቡቲ ወደብን ስትጠቀም ትከፍለው የነበረው ቀረጥ እንዲቀር እና በነፃ እንድትጠቀም የፈረንሳይ መንግስትን ስምምነት ላይ እንዲደርስ አደረጉ፡፡
– “ ……. ፈጣን ወጣት ነበረ!!!……” ይላሉ:: – የሀገራችን የቱሪዝም ታሪክ ሲወሳ ስማቸው የሚነሳውን አቶ ሐብተስላሴን ሲገልፁ ፡፡ ልኡል ራስ መንገሻ ስዩም የሀገራችንን የቱሪዝም እምቅ ሀብት በሚገባ ስለተረዱት ፤ ጀርመኖች የቴክኒክ ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው አድርገው አቶ ሐብተስላሴን የቱሪዝም ቢሮን እንዲመሩ ሀላፊነት ሰጧቸው፡፡
– ሰላሌ እና ኦጋዴንን በመሳሰሉ የሀገራችን ከተሞች በአሰሯቸው ትምህርት ቤቶች ተምረው ለትልቅ ደረጃ የበቁ – ቤት ይቁጠራቸው፡፡ አሻራቸውን በአሳረፉባቸው ክሊኒኮች ተፈውሰው – ስለ መልካም ተግባራቸው ዛሬም የሚመሰክሩላቸው በርካታ ዜጎች ናቸው፡፡
– ትግራይ!!!…….
ልኡል ራስ መንገሻ ስዮም ትግራይን ለማስተዳደር መቐለ የገቡት በ1953 ዓ.ም እነ ጄኔራል መንግስቱ ነዋይ ባካሄዱት መፈንቅለ መንግስት አባታቸው ራስ ስዩም መንገሻ ከተገደሉ በኋላ በወርሀ ግንቦት ነበር፡፡ ቅድመ አያታቸው አፄ ዮሐንስ – ጮምዓ ኮረብታ ላይ ድንኳን ደኩነው የመሰረቷት ከተማ – መቐለ
አፄ ዮሐንስ ለሀይማኖታቸው ቀናኢ ቢሆኑም የግለሰቦችን የእምነት ነፃነትን አክባሪ መሆናቸውን ለመረዳት የእስልምና ተከታዮች እንዲሰፍሩበት እና በነፃነት እንዲንቀሳቀሱበት መቐለ ውስጥ የመሰረቱት ዓዲ እስላምን (የእስላም መንደር) መጎብኘት በቂ ማስረጃ ነው፡፡
መቐለ አሁን የያዘችውን ቅርፅ እንድትይዝ ያደረጉት ልኡል ራስ መንገሻ ስዩም ናቸው፡፡ ፕላን ተሰርቶላት – የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ዘርግተውላታል፡፡
ትግራይ ካሏት የቱሪስት መስህብ ውስጥ የአክሱም ፅዮን ቤተክርስትያንን እጅግ ማራኪ አድርገው ሲሰሩት መቐለ ያለው ነባሩ መስጊድም (04 ቀበሌ የሚገኘው) እንዲታደስ አድርገዋል፡፡
ልኡል ራስ መንገሻ እጅግ በርካታ መንገዶችን – ድልድዮችን ሰርተዋል፡፡ ህዝቡን እያሳተፉ ፤ ሰርተው እያሰሩ ትግራይን አስተዳድረዋል፡፡ እንደ ተራ ሰራተኛ የመንገድ ስራ ላይ ቡልዶዘር ሲያሽከረክሩ – ከአለቶች ጋር ሲታገሉ ላያቸው “ ገዥ!!!………….” የሚለው ቃል – ትርጉሙን ያጣል፡፡
“ የሰለጠነች ነች!!!…….” በሚባልላት እንግሊዝ ውስጥ – አንድ ልኡል እራሱን ዝቅ አድርጎ እንደ ተራ ዜጋ ሰርቶ ለማሰራት በመሞከሩ ቤተሰቦቹ “ ክብራችንን አዋረድክ!!!…….” በሚል የቤተሰብ አካል መሆኑን እንደካዱ አንድ ወዳጄ አጫውቶኛል፡፡ ታድያ – ኋላ ቀር አስተሳሰብ በእጅጉ በሚንፀባረቅባት ኢትዮጵያ ልኡል ራስ መንገሻ እንዲህ ሰርተው ሲያሰሩ “ ………..ምናልባት – ልኡሉ ከትውልዶች ቀድመው ተፈጥረው ይሆን?……………” የሚል ጥያቄ ያጭራል፡፡
ፎቶዎችን ስመለከት “ ገዥ!!!……..” እንደዚህ ተራ ልብስ ለብሶ የሚሰራ ከሆነ “ ፕሬዚዳንት – ሚኒስትር!!!……..” ምናምን የሚባሉት ስልጣኖች “ ገዥ!!!……….” እንዲባሉ ተመኘሁ፡፡ ሰርተው ሳያሰሩ ውጤት የሚጠብቁ – ደሀ ሀገር ይዘው ሁሌም ከረቫት የማይለያቸው የፕሮቶኮል አቀንቃኞችን ሰብስበው – ልኡል ራስ መንገሻ ስዩም ስለ ስራ 101 ኮርስ ቢጤ እንዲሰጧቸው አሰብኩ፡፡
የትግራይ ልማት ድርጅት እና በርካታ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን መስርተው ከህዝቡ ጋር ተንቀሳቅሰዋል፡፡ – የደሀ ፤ የወላጅ አልባ ህፃናት አባት – ልኡል ራስ መንገሻ ስዩም፡፡
ይገርማል!!!………. ልኡል ራስ መንገሻ ሁለገብ ናቸው፡፡ ሙዝየም በሚመስለው – መኖሪያ ቤታቸው ግድግዳ ላይ ከተሰቀሉት ፎቶዎች ውስጥ አንዱ – በገመድ ጉተታ የስፖርት ውድድር ሲሳተፉ ያሳያል፡፡ ሌላ ፎቶ ተመለከትኩ፡፡ – በወቅቱ ከነበሩት የ “ መሶቦ ” እና የ “ ታይድል ” ስፖርት ክለቦች ጋር በጠንካራ ተፎካካሪነቱ የሚጠቀሰው የ “ እንደርታ ” እግር ኳስ ክለብ ውስጥ በአጥቂ መስመር ተጫዋችነት ተሰልፈው ስመለከት ገረመኝ፡፡
“ ጎበዝ ተጨዋች ነበርኩ!!!……….” አሉኝና በትዝታ ፈረስ ወደ ኋላ ሽምጥ ጋለቡ፡፡
ልኡል ራስ መንገሻ በስራቸው ከሀገር ውስጥ እና ከተለያዩ ሀገራት ልዩ ልዩ ሽልማቶች ተበርክተውላቸዋል፡፡ ሽልማቶቻቸውን እያሳዩ ሲዘረዝሩልኝ – አንዱን ፤ ትልቁ ሽልማታቸውን ግን አልጠቀሱልኝም፡፡ – የሚዳሰስ ስላልሆነ ይሆን?………. እኔ ግን አይቸዋለሁና ሽልማታቸውን እጠቅሳለሁ፡፡ – በህዝብ ልብ ውስጥ የተሰጣቸው – የክብር አክሊል፡፡
ደርግ ስልጣን እንደተቆናጠጠ የአስራ ሶስቱ ጠቅላይ ግዛቶች ገዥዎችን ወድያው በቁጥጥር ስር ሲያውል ልኡል ራስ መንገሻን ግን – በህዝብ ውስጥ ያላቸውን ተቀባይነት ስለሚያውቅ ሊይዛቸው ህዝብን በመፍራት ሲያመነታ ነበር – አምልጠው ወደ ስደት የወጡት፡፡
ዛሬም – ይሰራሉ፡፡ዛሬም – በተለያዩ የልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥ የነቃ ተሳትፎ ያደርጋሉ፡፡ ዛሬም – በዚህ እድሜአቸው ድንጋዮችን እየፈለፈሉ የሰሯቸውን የአክሱም ፤ ላሊበላ ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ቅርፆችን ስመለከት ከልቤ አደቅኳቸው፡፡ – ዛሬ ላይ እንዲህ – የጎረምሳ ጥንካሬን የተላበሱበት ሚስጥር – የስራ ወዳድነታቸው ይሆን?
ከሰሯቸው ቅርፃ -ቅርፆች ውስጥ የቅድመ-አያታቸውን አፄ ዮሐንስን ትኩር ብለው ሲመለከቱ እና ሲተክዙ አስተዋልኳቸው፡፡
ሁለቱንም አሰብኳቸው፡፡ ለሀገራቸው ብዙ ደክመው – በመንግስትም ፤ በሚድያም ተገቢው ክብር ያልተሰጣቸው – ነገር ግን ህዝብ በልቡ ያከበራቸው ጀግኖች፡፡ – በህዝብ ልብ ውስጥ መንገስ ምንኛ መታደል ነው?
ድምፄን ዝቅ አድርጌ – አጉተመተምኩ፡፡ አፄ ዮሐንስ – ልኡል ራስ መንገሻ ስዩም ተገቢው ክብር እስኪሰጣቸው – ድረስ መፃፌን – መጎትጎቴን እቀጥላለሁ፡፡ የአፄ ዮሐንስ አፅማቸውን መፈለግ – ማሰፈለጌን እቀጥላለሁ፡፡ ቃል ገባሁ፡፡ – በመሀላ
ዮሐንስን!!!
የማቱሳላ እድሜን ከጤና ጋር ገምዶ ለልኡል ራስ መንገሻ ስዮም እንዲሰጥልኝ አምላክን እለምናለሁ፡፡
በመጨረሻም!!!……… በየትኛውም ስርአት ውስጥ ሆነው ለሀገር ጠቃሚ ታሪክ የሰሩ ግለሰቦችን እውቅና እና ክብር መስጠት ለነበሩበት ስርአት ክብር መስጠት አይደለም፡፡ እንዲህ አይነት አስተሳሰብ ምንጩ የእይታ ብዥታ ነው፡፡
ወዳጆቼ!!!……….ከዚህ አይነት ሸውራራ አመለካከት ለመላቀቅ ዝግጁነታችሁን በመሀላ አረጋግጡልኝማ!!! እኔም – እነሆ መሀላዬ
ዮሐንስን!!!

You may also like...