Jesus-Painting

የሰማይና የምድር ያህል የተራራቀ የፖለቲካ ፍላጎቶች ያላቸው ሀይሎች የፈፀሙት ጋብቻ ለኦሮሞ ህዝብ ከመቆርቆር የመጣ አይደለም – ምሁራን

Jesus-Painting

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 8፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የእድሜ ስፍራቸው ሶስት መንግስታትን ያሳያቸው አዛውንት አቶ ድርቢ በርባዳ ስለ ሰላም ታናናሾቻቸውን ቢናገሩና ያጠፉትን ቢገስጹ ያምራል።

ሰላም ባልነበረበት በዚያኛው ዘመን ከውሃ ጥማት በላይ የበረታው የሰላም ዋጋን ተጠምተው አይተውታል።

ያ አስጨናቂው ዘመን ከታለፈበት የኋላ ታሪክ ምእራፍ ዳግም ተገልጦ ዛሬ ላይ ሊመለከቱት አይሹም፤ ይህ ፍላጎት የእኚህ የእድሜ ባለጸጋ አባት ብቻም አይደለም።

ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ ከተሞች በተፈጠረው አለመረጋጋት ሰላምን ለመሻት ትናንት በለገጣፎ ከተማ በተጠራው የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት የሀይማኖት አባቱ ሀጂ ያሲን ሸሪፍ መልዕክትም ተመሳሳይ ነው፡፡

በህዝቡ የተጠየቀውን የግልጽነትና የመብት ጥያቄ ጠልፎ በመውሰድ ሰላምን ለመንጠቅ የሚሯሯጡትን አይሆንም ልንላቸው ይገባል ብለዋል፡፡

የሀይማኖት አባቶቹ ህብረተሰቡ ልጆቹን መምከር አለበት ያሉ ሲሆን፥ እኛ የሀይማኖት አባቶችም በየእምነት ተቋማት በማስተማር ጥያቄዎቹ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲመለስ ማድረግ አለብን ነው የሚሉት።

እነዚህ ለጥፋት ነጋሪት የሚመቱ ከሰላም ይልቅ ሁከትን፣ ከመቀራረብ ይልቅ መለያየትን የሚሰብኩ የጥፋት ልኡካን፣ ቀድሞ ነገር ጠበቃው ነን ለሚሉት የኦሮሞ ህዝብ የሚመጥን መቆርቆርን ከወዴት አመጡት ሲሉ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ዶክተር ሙሉጌታ ደበበ ይጠይቃሉ፡፡

ይህ በየትኛውም አጋጣሚ ስርአት አልበኝነትን በማስፈን በሚፈሰው ደም ተረማምደው በሚናፍቁት የስልጣን ጫፍ ላይ ለመድረስ የሚደረግ ሩጫ መሆኑንም ይናገራሉ፡፡

እሳቸው በትምህርት ካለፉበት የፖለቲካ ሳይንስ እሳቤም ሆነ ከአለም አቀፍ እውነታ የሰማይና የምድር ያህል የተራራቀ የፖለቲካ ፍላጎቶች ያላቸው ሀይሎች አብረው መቆም ከጀመሩ እንታገልለታለን ለሚሉት አላማ መታመንን ረስተዋል ነው የሚሉት፡፡

ለእነዚህ ሰዎች ጉዳያቸው አንድና አንድ ብቻ ነው፤ ያም የተገኘውን አጋጣሚ መጠቀም ሲሆን፥ አሁንም የታየውም ይኸው ነው ብለዋል፡፡

ኦሮሞ እንደ ህዝብ ባህል እና ቋንቋውን ያከበረ ማንነትን ከማይቀበሉ ሀይሎች ጋር ለድጋፍ መጠሯሯጥ አላማው የተገነባውን ማፈራረስ የከበረውን ሰላም ማደፍረስ ብቻ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ያ ባይሆንማ የኦሮሞ ህዝብን ማንነት ከሚክዱ ሀይሎች ጋር ባልተቀደሰ ጋብቻ ለመሞሸር ባልተጣደፉ ይላሉ።

ዶክተር ሙሉጌታ አክለውም፥ ያለ ሀይላቸውን አቀናጅተው የማይገናኙ የትምክህትና የጥበት ሀይሎች በፍጹም ሊዛመዱ የማይችሉ ሀይሎች አንድ ላይ ሆነው ነው በዚህ ስርዓት ላይ ዘመቻ ያወጁት።

ሀይሎቹ ምንም የሚወክላቸው ድርጅትም ይሁን ዝግጅት የሌላቸው ናቸው ሲሉም ዶክተር ሙሉጌታ ያብራራሉ።

ሶስት እና አራት አባላትን ፓርቲ ነኝ ብሎ ሀገር መምራት አይችልም፤ በዚህ መልኩ የሚቋቋሙ ሀይሎች ግባቸው ሀገሪቱን ማፍረስ ብቻ ነው ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የወሊሶው ነዋሪ በበኩላቸው ይህን ኪሳራን እንጂ ትርፍን የማያውቅ ስሌት ውድመትን እንጂ ልማትን የማይጠራ የኋልዮሽ ጉዞን ማስቆም የእኛ የሀገር ሽማግሌዎች ሀላፊነት ነው ብለዋል።

አሁንም የምንመካበትን ሰላም ዳግም ከስፍራው ለመመለስ የሁላችንም ወላጆች ሀላፊነት መሆን አለበት ብለዋል፡፡

በተለያዩ የክልሉ አከባቢዎች የተጀመሩ ግልጽ ውይይቶችም በተሳሳተ የጥፋት ቅስቀሳ በስህተት ጎዳና የተራመዱትን በርካቶችን ወደ ሰላማዊው መንገድ ለመመለስ እድል ፈጥሯል፡፡

You may also like...