Fields-On-Tis-Isat

የህዝቡን ጥያቄ ተገን አድርገው ወደ ውንብድናና ስርአት አልበኝነት የገቡ አካላትን ስርአት የማስያዝ እርምጃው እንደሚቀጥል መንግስት ገለጸ

በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች የተነሱ የህዝብ ጥያቄዎች መልካም አስተዳደርን በማስፈን የሚመለሱ መሆናቸውን መንግስት ገለጸ።

ሰሞኑን በሁለቱ ክልሎች አንዳንድ ቦታዎች የተከሰተውን ሁኔታ አስመልክቶ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሀላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

ሚኒስትሩ በመግለጫቸው በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች በነዋሪዎች እና ተማሪዎች የተነሱ ጥያቄዎች ነፃ ዜጋ የሚያነሳቸው ተገቢ ጥያቄ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ጥያቄዎቹ መረጃ የሚጠይቁ በመሆናቸው አገሪቱ ያላት ስርዓት በሚፈቅደው መሰረት ህጋዊ በሆነ ዴሞክራሲያዊ አግባብ ሊቀርቡ የሚችሉ እና ምላሽም የሚያስፈልጋቸው የህዝብ ጥያቄዎች ናቸው ነው ያሉት።

ነገር ግን ጥያቄዎቹ ተገፍተው ወደ አደባባይ ጩኸት እና ሁከት በመቀየራቸው ፀረ ሰላም ሀይሎች ውስጣዊ የሆነውን የህዝብ ትክክለኛ ጥያቄ በመጠቀም ከጀርባ ሁከት ለመፍጠር እድል እንደሰጣቸውም ነው አቶ ጌታቸው ያስረዱት።

መንግስት ምላሽ ሊሰጥበት ይችል የነበረው የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ማስተር ፕላን ጥያቄ መልኩን መቀየሩን አንስተው፥ ጉዳዩ የተደራጀ ሽብር ወደ መንዛትና ወደ ግድያ እየገባ መሆኑን ጠቁመዋል።

የተቀናጀው ማስተር ፕላን ከዚህ በፊት ጥያቄ ቀርቦበት ለጊዜው አተገባበሩ በዘገየበት እና ከህዝብ ጋር ውይይት ተደርጎበት ለመተግበር ምንም እንቅስቃሴ ባልተደረገበት ሁኔታ እንዲሁም፥ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የክልሉን ከተሞች ለማልማት ያወጣው አዋጅ ከዚህ ማስተር ፕላን ጋር ግንኙነት ሳይኖረው ሁከት ቀስቃሾቹ ረብሻውን የፈለጉት ለሌላ ምክንያት መሆኑን ነው ያስረዱት።

ይህ ሁኔታም በሞዴል ገበሬዎች፣ አርዓያ አመራሮች፣ ሌሎች ብሄሮች እና ሃይማኖቶች እንዲሁም የህዝብና የመንግስት ተቋማት ላይ የተደራጀ ጥቃት እስከ መሰንዘር መድረሱን ገልጸዋል።

ጥያቄውን ያነሱ ተማሪዎች እና ወላጆቻቸው ጥያቄውን በትክክለኛ መንገድ አቅርበውና ጉዳዩን በሰከነ መንፈስ በመመልከት ተገቢውን መንገድ ሲመርጡ፥ አላማቸው የህዝቡን ጥያቄ በማጣመም የግል ፍላጎታቸውን ማሳካት የሆኑት እነዚህ ኃይሎች ደግሞ ብጥብጥና ሁከትን ምርጫቸው አድርገዋልም ነው ያሉት።

መንግስትም የህዝቡን ጥያቄ ተገን አድርገው ወደ ውንብድናና ስርአት አልበኝነት የገቡትን እነዚህን አካላት ስርአት የማስያዝ እርምጃውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

ሚኒስትሩ እንደገለፁት አሁን አብዛኛው ህዝብ ከሁከት የተላቀቀ ውይይትን መርጦ ከክልሉ መንግስት ጋር እየተወያየ በመሆኑ፥ ሁከት የተቀሰቅሰባቸው አካባቢ ነዋሪዎች ጉዳዩን በሰከነ መንፈስ መመልከት ጀምረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ከማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ተነስቶ የነበረው የቅማንት ብሄረሰብ ጥያቄ በተደረገ ውይይት መፈታቱንም አውስተዋል።

መንግስት የኦሮሚያ ክልል ህዝብን ጨምሮ ሁሉም ኢትዮጵያ አደራ የሰጠውን እና ሊፈታው በይፋ ቃል የገባለትን የመልካም አስተዳደር ችግር በዓይነቱ እና በዝግጅቱ ሰፊ ዘመቻ እየጀመረ መሆኑን አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።

ዘመቻውም ለመልካም አስተዳደር የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ምክንያት የሆነውን የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከቶችን እና ተግባራትን በህዝብ ተሳትፎ የሚበጣጥስ መሆኑም ተነስቷል።

በመንግስት መዋቅር እና በህዝቡ ውስጥ የተደበቁ ኪራይ ሰብሳቢዎችን የሚያጋልጠው ዘመቻው በህዝብ ላይ የተጫኑትን የአክራሪነት፣ የጥበት፣ የትምክህትና የሙስና መደበቂያ ከሆነው የመልካም አስተዳደር ችግር ህዝቡን ነፃ የሚያወጣ መሆኑንም ነው የገለፁት።

በሀይማኖት እና በብሄር ስም ህዝብን እያወናበዱ ኪራይ የሚሰበስቡ ጥገኞች የጥቅማቸው መሰረት ስለሚናድ ይህን ዘመቻ መፍራታቸው እንደማይቀርም አመላክተዋል።

ልማትን በፀረ ልማት መንገድ ማረጋገጥ እንደማይቻል በመጥቀስም እነዚህ የታጠቁ የውንብድና ሀይሎች በምንም መንገድ እንታገልለታለን ለሚሉት ህዝብ ሰላም ማስፈን እና ልማትን ማረጋገጥ እንደማይችሉ ተናግረዋል።

የህዝብ መገልገያዎች የሆኑ መሰረተ ልማቶች እና ተቋማት ላይ የደረሰው ጥቃትም ለህዝብ አለመቆምን ማሳያ መሆኑንም አስረድተዋል።

የሰላም እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የሚመለሰው በተደራጀና ህዝብ እምነት በጣለበት ልማታዊ መንግስት ብቻ መሆኑንም ነው የገለፁት።

በመሆኑም የተጀመረውን የመልካም አስተዳደር ችግር የመፍታት አቅጣጫን በማጠናከር የህዝቡን ጥያቄ የመመለስና ፀረ ሰላም እንቅስቃሴውን ማቆም እና መመከት ብቸኛው መፍትሄ እንደሆነም ነው የገለጹት።

ከሱዳን ጋር ድንበር ማካለል ሊደረግ ነው ተብሎ ስለሚናፈሰው ወሬ ምላሽ ሲሰጡም፥ ስለ ድንበር ማካለሉ ለአመታት ሲናፈስ የነበረ ሃሰተኛ መረጃ መሆኑን ገልጸዋል።

FBC

You may also like...