Ancient-Bible

የአገር ሰው ጦማር : ከነገስታቱ መንደር

በሙሔ ሐዘን ጨርቆስ (ለዋዜማ ራዲዮ ብቻ)

እንዴት ናችሁልኝ!? እኔ ያው ደህና ነኝ፡፡ ድሮስ ኮንዶምንየም የተመዘገበ ሰው ምን ይሆናል ብላችሁ ነው፡፡ ምን ቢማረር በመንግሥት አይጨክን!!

መቼ ለታ በ‹‹ሀይገር›› አውቶቡስ ወደ ‹‹ሲኤምሲ›› ተሳፍሬ ከሾፌሩ ጎን ጥቅስ አነበብኩ፡፡ ‹‹20/80 የተመዘገበና የተጠመቀ ዳነ›› ይላል፡፡ አልሳቅኩም፡፡ እንዲያውም ፈራሁ፡፡ አሽሙርና አሽሙረኛ ፈሪሃ እግዚአብሔር ባደረበት ሕዝብ መሐል ሲበዛ፣ ‹‹እረኛ ምን አለ›› የሚል ንጉሥ የመጥፋቱ ምልክት አድርጌ ስለምረዳው እፈራለሁ፡፡

ይህቺ ጥብሳ ጥብስ ስታጣ በጥቅሳ ጥቅስ የተዥጎረጎረች ከተማ አላማረችኝም፡፡ ‹‹ጠቃሾቿ›› በብዕር ፈንታ ‹‹ክሪክ›› ያነሱ ዕለት….ወየውላት፡፡ የታክሲ ወያላ ያለነገር አይሸሙርማ፡፡ የታክሲ ወያላ ስድብ ትቶ ባለቅኔ ሲሆን ለአንድ ታዳጊ አገር ጥሩ ምልኪ አይደለም፡፡ ጥቅሷ ኮርኩራኝ እንዲህ ስል ተቀኘሁ፡፡

ወያላ የወየነ ‘ለት፣

ያን ጊዜ ነው “ዋ” ማለት፡፡

ወያላ የወየነ ‘ለት፣

ተሳፋሪም አለቀለት፣ ወራጅም ጉድ ፈላበት፡፡

በዚህ የተመሰጠረ ቅኔ ዉስጥ ‹‹ወራጅ›› የሚለው ቃል ፍካሪያዊ ትርጉም ከሥልጣናቸው በሕዝብ አመጽ የሚወርዱ ሹመኞችን ያመለክታል፡፡ ይቺን ቅኔ ለከንቲባው ጽሕፈት ቤት መላክ አማረኝ፡፡ እውነት እውነት እላችኋለሁ ‹‹እረኛ ምናለ?›› የማይል ንጉሥ፣ ‹‹ወያላ ምን አለ?›› የማይል ከንቲባ ቢነግሡም ለመንፈቅ፣ ሲወድቁም መቀመቅ…፡፡

[ጦማሩን በድምፅ ሸጋ አድርገን አሰናድተነዋል አድምጡት]

ዉድ የጦማሬ አንባቢዎች!

አወዳደቃቸው የማያምር ነገሥታት አወዳደቃቸውን ለማሳመር የስፖንጅ ፍራሽ ሳሎናቸው ዉስጥ ቢዘረጉ ከስብራት ይድናሉ እንዴ? እንደኔ አወዳደቁ የማያምር ንጉሥ ከሕዝብ ርቆ ቤተ መንግሥት ለማስገንባት ጥልቅ ጉድጓድ ባያስቆፍር ነው የሚበጀው እላለሁ፡፡ ጉድጓዱ ዉስጥ ማን እንደሚገባበት አይታወቅማ፡፡ ንጉሥ ጋዳፊን ያየ በጥልቅ ጉድጓድ ቀርቶ በቦይስ ይቀልዳል እንዴ?!

ክቡራትና ክቡራን!

ለመንደርደር ያህል ይህን ካልኩ ዘንዳ….እስቲ ለዛሬ የኛዎቹ ነገሥታት ጥልቅ አስቆፍረው እያስገነቡት ያለውን ቤተ መንግሥት ላስቃኛችሁ፡፡ ለተራው ሕዝብ ሹክሹክታን የማይመክት የጋራ መኖርያ ቤት በ10 ዓመት አንዴ እየገነቡ በዕጣ የሚያድሉት ሹማምንት ለራሳቸው ሲሆን ‹‹ሳሎኑ ጎልፍ የሚያጫውት›› የጋራ ቤተ መንግሥት ገንብተው በመንፈቅ ይጠናቀቅላቸዋል፡፡ ለመሆኑን ስንቶቻችሁ በየካ ኮረብታ ላይ ስለሚገነቡት የተራራ እልፍኞች ታውቁ ይሆን?

ከሰላምታዬ ቀጥዬ የማስቃኛችሁ ነገር ቢኖር በአካል ተገኝቼ ያያሁትን ይህንኑ የነገሥታት ሠፈር ይሆናል፡፡

###

የማከብራችሁ አንባቢዎቼ ሆይ!

እስኪ ካላችሁበት ሰፈር ወደ ‹‹ሲ-ኤም-ሲ›› ምናባዊ ታክሲ ያዙ፡፡ የታክሲው ሰልፍ ከረዘመ ባቡር ተሳፈሩ፣ ባቡሩ ከሞላባችሁ ሞልቶ የማይሞላ 119 ቁጥር አንበሳ አውቶቡስ አለላችሁ፡፡ እንደምንም ራሳችሁን ከዉስጡ አኑሩ፡፡ ሰዎች ሆይ! በሕይወት መሳፈርን የመሰለ ደግ ነገር የለም፡፡ የነአባዱላን ሰፈር ጨምሮ ብዙ ያሳያል፡፡

ታስታዉሱ እንደሁ በሙስና የማይታማው ደርግ በመውደቅያው ዋዜማ ለራሱ ባይሆንም ለዲፕሎማቶች ቤት ገንብቶ ነበር፡፡ እነዚያ ቤቶች እስካሁንም የ‹‹ሴ-ኤም-ሲ›› ቤቶች ተብለው ይጠራሉ፡፡ እዚያ ጋር ስትደርሱ ‹‹ወራጅ!›› በሉ፡፡ እንደወረዳችሁ ፊታችሁን ወደ ሰሜን ስታዞሩ በኢትዮጵያ የመጀመርያ የሆነውን ዘመናዊ የከተሜ መንደር ወይም (Urban Complex) ታገኛላችሁ፡፡ ይህ ወደ ሰማይ እያረገ ያለ የሚመስለው ‹‹ፖሊሎተስ›› አፓርትመንት መንደር ‹‹ፀሐይ ሪልስቴት›› ይባላል፡፡ በ30ሺ ካሬ ቦታ ላይ 11 የሚሆኑ ሕንጻዎች እጅብ ብለው የቆሙበት ግቢ ነው፡፡

ምንም እንኳ የፖሊሎተስ ክፍሎቹ ከርቀት በተናጥል ሲታዩ እንደ ቻይናዊያኑ ዐይኖች ጠበብ ያሉ ቢመስሉም የአፓርትመንቶቹ ቁመና በአመዛኙ ዘለግ ያሉ መሆናቸው ለአካባቢው ልዩ ግርማን አላብሰውታል፡፡ ሦስት ቢሊየን ብር የፈጁት አፓርትመንቶቹ G+12 የሆኑ 17 ሕንጻዎችን ይዘዋል፡፡ ከ17ቱ አስራ አንዱ አሁን እየተጠናቀቁ ነው፡፡ እንዲያውም ልክ የዛሬ ሦስት ወር ለገዢዎች ይተላለፋሉ፡፡ ኤርሚያስ አመልጋ አንድ ቢሊዮን ብር ሰብስቦ በሰባት ዓመት ዉስጥ አንድ ክፍል ቤት አላስረከበም፡፡ ቻይና ዱዲ ሳትቀበል በዓመት ተኩል 646 ቤቶችን ሠርታ ልታስረክብ ነው፡፡ የቻይናን ልቦና ይስጠን አቦ!

###

ለመሆኑ ‹‹ፀሐይ ሪልስቴት›› የማን ነው? ስሙ ያወዛግብ እንጂ ሙሉ በሙሉ የቻይኖች ንብረት ነው፡፡ “የዉጭ ድርጅቶች በቤት ልማት ለመሳተፍ የሚያበቃቸው የሕግ አግባብ የለም” አልተባለም እንዴ?” እንዳትሉኝ፡፡ ‹‹ቻይና የዉጭ ዜጋ ናት እንዴ?›› እላችኋለሁ፡፡

Read more

You may also like...