አንዳርግ ያችን ሰዓት

By Sebat Kilo

(ዳኝነት መኮንን እና ማስረሻ ማሞ)

በመንገደኛው ፊት ላይ ማመንታት እና ጥርጣሬ ይታያል፤ ወደተጠሩበት መስኮት መሄድ የፈለጉ አይመስልም፤ የአየር ማረፊያው ተናጋሪ በድምጽ ማጉያው ደግሞ ደጋግሞ ስማቸውን ይጠራል። በጎልማሳነት ዕድሜ መጨረሻ ላይ የሚገኙት መንገደኛ ቀስ እያሉ ወደ መስኮቱ ተጠጉ። ቦታው ጋራ ደርሰው ለሰከንዶች ቆም ካሉ በኋላ ከመስኮቱ ጀርባ ከቆሙት አገልጋዮች መካከል ለአንደኛው ስማቸው መጠራቱን ገልጸው ለምን እንደተፈለጉ ጠየቁ። አገልጋዩ የመንገደኛውን ፓስፖርት ተቀበለ እና ፎቷቸውን ትክ ብሎ ተመለከተ። ከዚያም ምስሉን ፊት ለፊቱ ከቆሙት መንገደኛ ገጽ ጋር አመሳሰለ። ፓስፖርቱ ላይ ያለው ፎቶ መንገደኛው በ1999 ዓ.ም የተነሱት ነው። “አንዳርጋቸው ጽጌ ሀብተማርያም“ አለ አገልጋዩ ጉልበት በተቀላቀለበት ድምጽ። ከመስኮቱ ብዙም ሳይርቅ የተቀመጡ ኢትዮጵያዊ ተጓዥ ኹኔታውን በጥሞና ይከታተላሉ። “ እባክዎን ይከተሉኝ?”

ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ አንዳርጋቸው ጽጌ በየመን የጸጥታ ኀይሎች አስገዳጅነት የመንገደኞች ማመላሻ አውቶቡስ ውስጥ እንዲገቡ ተደርገው ሰንዐ አየር ማረፊያ ወደሚገኘው የጦር አውሮፕላን ማረፊያ ተወሰዱ። ብዙም ሳይቆይ በአነስተኛ አውሮፕላን እንዲሳፈሩ ተገደው፤ ከአንድ ሰዓት ከኀምሣ ሦስት ደቂቃ በረራ በኋላ ደብረ ዘይት አረፉ። የኢትዮጵያ መንግሥት ዋነኛ ተፈላጊ፣ ፍርድ-አምላጭ እና ነፍጥ ያነሳ የተቃዋሚ ቡድን መሪ በአገሪቱ የጸጥታ ኀይሎች እጅ ወደቁ። የስድስት ዓመት ክትትል ባልታሰበ ጊዜ በድንገት አበቃ።

ቀኑ ሰኔ 16፣ 2006 ዓ.ም ነው፤ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ግንቦት ሰባት ከመሠረቱ ስድስት ዓመታት። በእነዚህ ጊዜያት ቡድኑ ላይ እና ታች- ከፍ እና ዝቅ ብሏል። አንዳርጋቸው በውጣ ውረዱ በሙሉ ዋነኛ ተዋናይ ነበሩ። የቡድኑ የአደባባይ ኮከብ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ቢኾኑም አርኪቴክቱ ግን አንዳርጋቸው ነበሩ። የአንዳርጋቸው በየመን የደህንነት ሰዎች እጅ መውደቅ ሲሰማ የኹሉም ስሜት ንዴት፣ ቁጣ፣ ቁጭት፣ ዕድለ ቢስነት እና መጠቃት ነበር። ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ “አመመኝ፤ እንደ ወፈፌ አደረገኝ” ሲሉ የነበራቸውን ስሜት ይገልጡታል። የሥራ አስፈጻሚው አስቸኳይ ስብሰባ ተጠራ። የአመራሩ አባላት አቶ አንዳርጋቸው በኢትዮጵያ እጅ መውደቃቸውን ጠረጠሩ። በእርሳቸው መያዝ የሚመጡ ጥፋቶችን እና ስጋቶችን ለመቆጣጠር ጥረት መደረግ እንዳለበት አመራሩ ተስማማ። አንዳርጋቸው ኢትዮጵያ እንዳሉ ማረጋገጫ የተገኘው በተያዙ በነጋታው ከእርሳቸው ኮምፒዩተር ወደ ሌሎች የግንቦት ሰባት ባለሥልጣናት ኮምፒዩተሮች ስፓይዌሮች መላክ ሲጀምሩ ነበር። “ለምን? ለምን? ለምን?” የብርሃኑ ነጋ የቁጭት ጥያቄ ነበር።፡

አንዳርጋቸው በፒያሳ

ለምን? አንዳርጋቸው ጽጌ ኢሕአዴግ ቀን ከሌት የሚፈልጋቸው ቀንደኛ ጠላት ለምን ኾኑ? የመልሱን መጀመርያ ለማግኘት 11 ዓመታት ወደ ኋላ መጓዝ አለብን። በጥር ወር 1997 ዓ.ም አንዳርጋቸው ጽጌ አዲስ አበባ ገቡ። የመጡት በምርጫው “ቅንጅትን እርዳ” የሚል መልእክት ከጓደኛቸው ከብርሃኑ ነጋ ስለደረሳቸው ነበር። ወዲያውኑ የቀስተ ዳመና አባል ኾነው የፓርቲ ሥራ ጀመሩ። ለመሥራት የመረጧቸው የሚያንጸባርቁ እና ስምና ዝና የሚያስገኙላቸው ሥራዎችን ሳይኾን “አታካች እና አድካሚ፤ ግን ወሳኝ” የድርጅት ተግባራትን እንደነበር አሜሪካ ለሚገኝ አንድ ጓደኛቸው በጻፉት ደብዳቤ ገልጸዋል። አቶ አንዳርጋቸው ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው ጥቂት ወራት በፊት ለንደን ላይ ከብርሃኑ ነጋ ጋር ተገናኝተው ኢሕአዴግን በምርጫ መጣል አይቻልም ብለው እንደሚያምኑ ለፕሮፌሰሩ ነግረዋቸው ነበር። ይኹንና “ሞክረን፣ አሸንፈን፣ እምቢ አንወርድም ማለታቸውን እናረጋግጣለን እንጂ እጃችንን አጣጣፈን አንቀመጥም” ለሚለው የብርሃኑ ሐሳብ ዕድል ሊሰጡት ፈለጉ። ነገር ግን በቅንጅት ምርጫ ላይ መሳተፍ ብቻ ሳይኾን፣ ጠንካራ ድርጅታዊ አቋም ሊኖረው እንደሚገባ እምነታቸው ስለነበር የመጀመርያ ሥራቸው የቀስተ ደመና ወጣቶችን ማደራጀት ነበር።

ሥራቸውን የጀመሩት በፒያሳ አካባቢ ነበር። በጊዜው የዚህ አካባቢ የወጣቶች መሪ የነበረው ኃብታሙ በላቸው (ስሙ ለደኅንነቱ ሲባል ተቀይሯል) ለመጀመሪያ ጊዜ ቼንትሮ ኬክ ቤት ተገናኝተው የተጨዋወቱትን ያስታውሳል። “ኢሕአዴግ በምርጫ አይወርድም፤ ስለዚህ የዴሞክራሲ ትግል ረዥም ጊዜ መውሰዱ አይቀሬ ነው። ድርጅቱ ራሱን ለዚያ ማዘጋጀት አለበት።” ሲሉ የኢሕአዴግን ባሕርይ እና የብዙ አገሮችን ጸረ አምባገነንነት ትግል ተሞክሮዎች እያነሱ እንዳስረዱት ይናገራል። ኃብታሙ “ምርጫ፣ ምርጫ፣ ምርጫ ብቻ” የሚል እምነቱን አንዳርጋቸውን ካገኘ በኋላ ርግፍ አድርጎ ጣለ። ከሌሎች አባላት ጋራ በመኾን ቀስ በቀስ የቀስተ ደመናን ክንፍ አጠናከረ። አቶ አንዳርጋቸው ወጣቶቹን በየጊዜው እያገኙ እርሳቸው የጻፏቸው አደረጃጀትን የሚመለከቱ ጽሑፎችን እንዲያነቡ ይሰጧቸው ነበር። ነገር ግን የቴሌቭዥን ክርክር ከተጧጧፈ በኋላ ቅንጅት ከሕዝብ ከፍተኛ ድጋፍ በማግኘቱ በወጣቶቹ ዘንድ “በምርጫ እናሸንፋለን” የሚለው መተማመን እያገረሸ እና እየጨመረ መጣ። ብዙዎች መደራጀቱን ቸል ብለው በምርጫ ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመሩ። በሚያዝያ ወር መጀመርያ አንዳርጋቸው አምስት የወጣቶች መሪዎችን ፒያሳ ቲሩም አግኝተው ዐይናቸውን ከኳሷ ላይ ማንሳት እንደሌለባቸው ቢመክሩም ለጊዜው የወጣቶቹን ቀልብ አልሳቡም። እንዲያውም ብርሃኑ ነጋን እየጠቀሱ ምንም ነገር በድብቅ መሠራት እንደሌለበት መለሱላቸው።

አንዳርጋቸው እነዚህን ወጣቶች በተደጋጋሚ በማግኘት መወትወታቸውን አላቆሙም። ነገር ግን ሌሎች የድርጅት ሥራዎችን ይሠሩም ነበር። ከዚህ መካከል አንዱ ቅንጅትን የሚደግፉ ወጣት ፕሮፌሽናሎችን በሳምንት አንድ ጊዜ እያገኙ ስለ ትግል ስትራቴጂ እና ታክቲክ ማውራት ነበር። ከእነዚህ ወጣቶች መካከል አንዷ የዓለምዘውድ በቀለ ነበረች። ምናልባትም የዓለምዘውድ ዝናዋ የናኘው በጥቅምት ወር 1999 ዓ.ም ኢሕአዴግ ‘በሕቡዕ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ተሳትፈሻል” ብሎ ሊይዛት ሲያፈላልግ በአውሮፓ ኅብረት ዲፕሎማቶች እየተነዳች ከአገር ለማምለጥ ስትሞክር ሞያሌ ላይ መያዟ በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ኮሚሽን መካከል ፈጥሮት በነበረው የዲፕሎማሲያዊ ፍጥጫ ነው። ኢትዮጵያ የዓለምዘውድን ለማስመለጥ የሞከሩትን ዲፕሎማቶች በ24 ሰዓት ውስጥ ከአገር እንዲወጡ አደረገች። የአውሮፓ ኮሚሽን በበኩሉ ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በጠንካራ ቃላት የታጀበ ቅሬታውን የሚገልጽ ደብዳቤ ጻፈ። ይህን የተባራሪ አባራሪ ድራማ ዘ-ኢኮኖሚስት መጽሔት “ሶቭየት ስኩል” በሚል ርእስ ዘግቦታል። አሁን በአሜሪካ የምትኖረው የዓለምዘውድ በእነዚህ ከአቶ አንዳርጋቸው ጋር በሚደረጉ ስብሰባዎች በተሳተፈችባቸው ጊዜያት በሙሉ የሚገርማት የአንዳርጋቸው ትኩረት ለአንድም ጊዜ ያለመለወጥ እና ያለመዛነፍ ነው። ከሚያዚያ ሠላሳ የሕዝብ ማዕበል በኋላ እንኳ የሚያወሩት ስለመደራጀት ነበር። በየስብሰባው ወጣት ፕሮፌሽናሎችን “ኢሕአዴግ በምርጫ ቢሸነፍ ሥልጣን ይለቃል ብላችሁ ታምናላችሁ?” ብለው ይጠይቁ ነበር። ከተሳታፊዎቹ የሚያገኙት ምላሽ አጥጋቢ አልነበረም። የኢሕአዴግ ደኅንነት ይህን የአንዳርጋቸውን እንቅስቃሴ በጥንቃቄ ይከታተል ነበር። ባለሥልጣናቱን ያስፈራቸው ምርጫው ሳይኾን ከምርጫው በኋላ ሊከሰት የሚችለው ዐመጽ ነው። በዚህም ምክንያት የአንዳርጋቸው መደራጀት ላይ ማተኮር አስግቷቸዋል። ጋዜጠኛ ፋሲል የኔዓለም ከምርጫው በፊት መንግሥት ባዘጋጀው አንድ ስብሰባ ላይ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር የነበሩት ወይዘሮ ነጻነት አስፋው የሻይ ረፍት ላይ ከኢሕአዴግ ደጋፊ ጋዜጠኞች ጋር ሲያወሩ ጆሮውን ጣል አድርጎ ያዳምጥ ነበር። ወይዘሮ ነጻነት እጃቸውን እያወናጨፉ በቅንጅት ውስጥ በስውር መንግሥትን የመገልበጥ ዓላማ ስላላቸው ሰዎች ስም እየጠቀሱ ያስረዱ ነበር። “ከእነዚህ ሰዎች መካከል ዋነኛው እና በተደጋጋሚ ስማቸው የሚነሳው አቶ አንዳርጋቸው ነበሩ” ይላል ፋሲል። በርግጥም ለአቶ አንዳርጋቸው ኢሕአዴግ ውስጥ ካሉ ወዳጆቻቸው “ተቆጠብ፣ እየተከታተሉህ ነው” የሚል ማስጠንቀቂያ አዘል ምክር ይላክላቸው ነበር።

ዝዋይ

የሰኔ አንድ ግርግር ሲነሳ የኢሕአዴግ የደኅንነት ሰዎች ከሁሉ አስቀድሞ የሄዱት ቦሌ ወደሚገኘው ወደ አንዳርጋቸው ቤተሰብ ቪላ ነበር። ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ነው። በሩን አንኳኩተው ሲከፈትላቸው ወደ ውስጥ ገቡ። ግቢው ፈረስ ያስጋልባል። የደኅንነት አባላቶቹ ወደ ቪላው ሳያስፈቅዱ ከገቡ በኋላ በቀጥታ ያመሩት ወደ ትንሿ ክፍል ነው። በክፍሏ ውስጥ አንዲት ታጣፊ አልጋ ተዘርግታለች። መሬቱ እና የመጻሕፍት መደርደሪያው በፍልስፍና እና በፖለቲካ መጻሕፍት ተሞልቷል። አንዳርጋቸው ከሁሉም በላይ የሚመርጡት ፈላስፋ ቺ ዦን ፖል ሳርተ Sketch for a Theory of The Emotions በጠባቧ ጠረጴዛ ላይ በወረቀቶች ተከቦ ተቀምጧል። አንዳርጋቸው ሥራቸውን የሚሠሩት በዚች ትፍግፍግ ባለች ክፍል ነው። ደኅንነቶቹ ሰውየውን ሊያገኙ ባይችሉም ወረቀቶቻቸውን ሰብስበው ወጡ። ሌሎች ባልደረቦቻቸው አንዳርጋቸውን ከቤታቸው ብዙም ሳይርቁ መንገድ ላይ እንደያዟቸው ወደቤቱ ለገቡት ሰዎች በተንቀሳቃሽ ሥልክ ነገሯቸው። በሚቀትሉት ሁለት ሳምንታት አቶ አንዳርጋቸው በዝዋይ እስር ቤት በሺሕዎች ከሚቆጠሩ ሰዎች ጋር ታስረው ቆዩ። ሰውነታቸው ላይ ሰፈፊ ጠባሳዎች ያስቀረ ከፍተኛ ድብደባም ደረሰባቸው። ከእስር ቤት እንደወጡ በአስቸኳይ አገር ካልለቀቁ እንደሚገደሉ ተዛተባቸው። ቅዳሜ በወጡ ሦስት ጋዜጦች ላይ በቀረቡ ቃለ ምልልሶች የመጨረሻ የመለያያ የቃላት ጥይታቸውን ኢሕአዴግ ላይ አርከፍክፈው ከኻያ ዓመታት በላይ ወደኖሩባት ለንደን አቀኑ። ይህ የእስር ቤት ተሞክሯቸው የአንዳርጋቸውን እምነት ይበልጥ አጸናው። “ከእስር ቤት የወጣው አንዳርጋቸው የአሳሪዎቹን አረመኔነት በገሃድ ያየ፤ ቁጣውን ያናረበት፣ በእርሱ ላይ የደረሰውን ብቻ ሳይኾን በሌሎች ታሳሪዎች ላይ የሚሰደርሰውን ሰቆቃ እና መከራ ሊያይ፣ ሊያዳምጥ እና ሊሰቃይ በመገደዱ ነው።” ይላሉ ፕሮፌሰር ብርሃኑ። የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ኾነው የሚያውቋቸው አቶ ያሬድ ጥበቡ የሰኔ አንዱ እስር በተለይ ደግሞ ከዱላው በላይ ጸያፍ ስድቦቹ “አዕምሮውን የመረዙት ይመስለኛል” ይላሉ።

አቶ አንዳርጋቸው ብዙም ሳይቆዩ የቃላት ተኩሳቸውን ወደ ተግባር ተኩስ ለመለወጥ መንቀሳቀስ ጀመሩ። ሐምሌ 19 ቀን 1997 ለሀብታሙ እና ለሌሎች ወጣቶች ባለ ሃምሳ ገጽ ዶኩዩመንት በኢሜይል ደረሳቸው። የኢሜይሉ ምንጭ ለንደን፤ ጸሐፊው አንዳርጋቸው ነበሩ። ከምርጫው በኋላ እነዚህ ወጣቶች የአንዳርጋቸው ትንበያ ጠብ እንዳላለ ተረድተዋል። ኢሕአዴግ በምርጫ ሥልጣን እንደማይለቅ፣ ቅንጅት ድርጅቱን ማጠናከር እንዳለበት አምነዋል። ነገር ግን የቅንጅት መሪዎች በምርጫ ውዝግብ ተጠምደዋል። ከአመራሮቹ መካከል አብዛኞቹ ከምርጫ ውጪ ላለ ትግል ‘አፒታይት’ አልነበራቸውም። የአንዳርጋቸው 48 ገጽ ሰነድ የሚያወራው ስለ ሕቡዕ እና ከፊል ሕቡዕ አደረጃጀት ነው። ሀብታሙ ሰነዱን ካነበበ በኋላ የኢሜይል ምላሹን ሰጠ፤ “በተጠቀሱት ሐሳቦች ተስማምቻለሁ፤ ነገር ግን ይህ አደረጃጀት በቅንጅት ውስጥ መኾን የለበትም፤ ፓርቲው የመሰነጣጠቅ አደጋ እንዳለበት አንተም ከዚህ በፊት ባደረግነው የኢሜይል ልውውጥ ተስማምተኻል። ከዚያ በተጨማሪም የቅንጅት ሰዎች እንዲህ ዐይነት የተደራጀ መራር ትግል ለማድረግ የሚፈልጉ አይመስለኝም። ስለዚህ እኔ የምመርጠው ፓርቲውን ወደ ጎን አድርገን መደራጀትን ነው” ይላል ደብዳቤው።

ከአቶ አንዳርጋቸው የመጣው ምላሽ የሀብታሙን ስጋቶች በጥቅሉ የሚቀበል ነገር ግን ሕቡዕ እና ከፊል ሕቡዕ አደረጃጀቱ በቅንጅት ሥር እንዲኾን የሚገፋፋ ነበር። “እኔ አንዳንዶቹን አመራሮች ደውዬ ይህን አደረጃጀት እንዲቀበሉ እወተውታቸዋለሁ፤ ያንተው” ይላል የምላሹ መደምደሚያ። ለሚቀጥሉት ሁለት ወራት አቶ አንዳርጋቸው ከቅንጅት መሪዎች መካከል ለሚቀርቧቸው እየደወሉ ስለ አደረጃጀት ለማውራት ቢሞክሩም ብዙም አልተሳካላቸውም። መሪዎቹ በውስጥ ቁርቁስ፣ ከኢሕአዴግ በሚመጣባቸው እንግልት እና በሕዝብ እና በተቃዋሚ ሚዲያ በሚደርስባቸው ጫና ምክንያት የመተንፈሻ ጊዜ አልነበራቸውም። እነዚህ መሪዎች መስከረም 13 ከተፈረመው የቅንጅት ውህደት በኋላ ፋታ ያገኛሉ ተብለው ቢጠበቁም ውህደቱ ከተደረገ በኋላ ድርጅቱ “ማኅተም ስጥ – አልሰጥም እና ፓርላማ እንግባ- አንግባ” በሚሉ ውዝግቦች ተጠመደ። የውስጥ ተቃርኖና ልዩነቶቹ እየጎሉ መምጣት ጀመሩ።

የውስጥ ትንቅንቅ

በመስከረም 1998 ዓ.ም መጨረሻ አንዳርጋቸው የሀብታሙን ምክር ተቀብለው የቅንጅትን ተዋረድ ትተው ሕቡዕ ቡድኖችን ማደራጀት ጀመሩ። የቅንጅት መሪዎች ከታሰሩ በኋላ በተለይ በአዲስ አበባ በሥውር ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ ቡድኖች መካከል አብዛኞቹ በአንዳርጋቸው የተደራጁ ወይም ከአንዳርጋቸው ጋራ ንክኪ የነበራቸው ነበሩ። ከእነዚህ መካከል ሁለቱ በጥር ወር 1998 በኢሕአዴግ የደኅንነት እና የጸጥታ ሰዎች በተደረገ መጠነ ሰፊ ጥቃት ፈራረሱ። አባሎቻቸው እስር ቤት ታጎሩ። የእነ ሀብታሙ ቡድን የዚህ ጥቃት ሰለባ ባይኾንም በገንዝብ እና በሀብት (resourse) ችግር ተዳከመ። ይህ አቶ አንዳርጋቸውን ወደማይወዱት የፓርቲ ውስጥ ትግል አመጣቸው።

በአሜሪካ እና አውሮፓ ከምርጫው በፊት የተቋቋሙ የቅንጅት የድጋፍ ምዕራፎች ከደጋፊዎች በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠር ዶላር ሰብስበዋል። ከእነዚህ ምዕራፎች መካከል በርካቶቹ በአቶ ኀይሉ ሻውል የሚመራው የመኢአድ አባለት እና ለኢንጂነሩ ታማኝ የነበሩ ናቸው። የቅንጅት ሕቡዕ መሪ የነበሩት አቶ አባይነህ ብርሃኑ በሕዳር ወር 1998 ሲታሰሩ ዳያስፖራ ባሉ ምዕራፎች አገር ውስጥ ባሉ ስውር ቡድኖች መካከል ያለው ግንኙነት ተቋረጠ። “የቅንጅት አመራሮች ከታሰሩ በኋላ እዚህ አሜሪካ ውስጥ ዋሽንግተን አካባቢ ብዙ መዝረክረክ ነበር። የቅንጅት አባል ድርጅቶ የነበሩትን አራቱን አባላት ወደ አንድ ቡድን ለማምጣት እንኳ ሥራ አልተጀመረም፤ መሪዎቹ እስኪታሰሩ ድረስ። ከታሰሩ በኋላ ሙከራዎች ቢደረጉም የመጠራጠር ኹኔታዎች ስለነበሩ ምቹ አልነበሩም” ይላሉ አቶ ያሬድ ጥበቡ። የአገር ውስጥ ቡድኖች በገንዘብ እጥረት ሲንኮታኮቱ የዳያስፖራ ደጋፊ ምዕራፎች በርካታ ገንዘብ ባንክ ውስጥ አስቀምጠዋል። አቶ አንዳርጋቸው የቅንጅት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበረው አቶ ዳንዔል አሰፋ እና የቻምበር ኦፍ ኮሜርስ የቀድሞው ፕሬዝዳንት አቶ ብርሃነ መዋ ይኼ ተቀማጭ ገንዘብ አገር ውስጥ ላሉ እንቅስቃሴዎች እንዲውል ጥረት ማድረግ ጀመሩ። አቶ አንዳርጋቸው ለቅንጅት አመራሮች (በተለይ ለብርሃኑ ነጋ) የኹኔታዎች ትንተና መላክ ጀመሩ። ብርሃኑ ነጋ በኤኤንሲ አደረጃጀት ተሞክሮ ትግሉን የሚመሩ የውጪ አገር አመራሮች እንዲኖሩ መጀመርያ ጥቆማ፣ ከዚያ ትዕዛዝ ሰጡ። አቶ አንዳርጋቸው የዚህ የአመራር ቡድን አባል ኾኑ። ይኹንና በመኢአድ ሰዎች በእነ አንዳርጋቸው መካከል በተነሳ ጸብ ሁለት የውጪ አመራር ቡድኖች ተፈጠሩ። አንደኛው የቅንጅት ኢንተርናሽናል ሊደርሺፕ ሲባል፣ ሌላኛው የቅንጅት ኢንተርናሽናል ካውንስል የሚል ስያሜ ያዘ። በሁለቱ ቡድኖች መካከል የነበረው እሰጥ አገባ እና ጦርነት የጦፈ ስለነበር አንዳንዶች በሹፈት “ኪል እና ኪክ” እያሉ ይጠሯቸው ነበር። በተለይ የሰሜን አሜሪካ ምዕራፎች ድጋፍ ተከፋፈለ። ጦርነቱን በቅርቡ የታዘቡ አንዳንድ ሰዎች አቶ አንዳርጋቸውን ክፉኛ ይነቅፋሉ። “የራሱን ፍላጎት ለማስጠበቅ ሲሞክር እንዳልተገራ ፈረስ ነው፤ መቆጣጠር አይቻልም፤ ወይ የፈለገውን ያገኛል ወይ ያጠፋል” ይላሉ አንድ የዋሽንግተን ዲሲ ምዕራፍ አመራር አባል የነበሩ። አቶ ያሬድ እንዲህ ይላሉ፦ “ስለ አንዳርጋቸው ሲወራ መካድ የማይቻለው ነገር ሲሰራ እንደ ጥማድ በሬ ነው። ጉልበት አለው፤ ጽናት አለው፤ ቁጭ ካለ አይነሳም፤ ጥልቅ እና ጠንካራ ስሜት አለው፤ ለሚሠራው ነገር በሙሉ። ለምሳሌ የእኔ ባለቤት የታወቀች ባለሞያ ነች። ነገር ግን እበልጥሻለሁ ብሎ ይከራከራል። በርግጥ እርሱ የሚለውን ያህል ባይኾንም ከብዙዎቻችን ይሻላል። ለያዘው ነገር በሙሉ እንደዚያ ይመስለኛል። በኪክ – ኪል ግጭት ዘመን እኔ ማስታረቅ ይሻል ይኾናል ብዬ አቶ ኀይሉ ከመሠረቱት ሰዎች ጋር ሥራ ስጀምር በጥልቅ ስሜት ነበር የጠላኝ፤ እንደሰማኹት ለሰዎች ስልክ እየደወለ በጣም ማመን የሚያስቸግር ዐይነት የጥላቻ ነቀፋዎችን ይሰነዝርብኝ ነበር። ይህ የእርሱ ማንነት ነው።”

አንዳርጋቸው ያሉበት የቅንጅት ዓለም አቀፍ አመራር ከሰሜን አሜሪካ ምዕራፎች መካከል የከፊሎቹን ድጋፍ እና ገንዘብ አገኘ፤ በውዝግቡ ስማቸው ጭቃ ውስጥ ቢዘፈቅም አቶ አንዳርጋቸው የሚፈልጉትን አገኙ። ለእነ ኃብታሙ እና ሌሎቸ ሕቡዕ ቡድኖች ገንዝብ መፍሰስ ጀመረ። ተዳክሞ የነበረው እንቅስቃሴ ነፍስ ዘራ። በ1998 ዓ.ም የክረምት ወራት ዶክተር ብርሃኑ እስር ቤት ኾነው የጻፉት “የነጻነት ጎህ ሲቀድ” ታትሞ መውጣቱ ከውጪ ከሚመጣው ገንዘብ ጋር ተደምሮ የሕቡዕ ቡድኖች አባላትን መንፈስ አጠናከረው፤ ጉልበት ሰጣቸው። “መሪዎችን ለማስፈታት እየታገልኹ ነው፤ እርስዎስ?” የሚል 13 ዐይነት የሠላማዊ አለመታዘዝ ታክቲኮችን በመጥቀስ የተቃውሞ ጥሪ የሚያደርግ ካሌንደር ታትሞ በከተሞች በሰፊው ተሰራጨ። ዘ-ኢኮኖሚስት መጽሔት በኦክቶበር 2006 ኢትዮጵያ ውስጥ የተስፋፋውን ተቃውሞ በተመለከተ ባወጣው ጽሑፍ በግነት “የመንግሥት ሥልጣን እየተነቃነቀ ነው” ሲል የብርሃኑ መጽሐፍ እና ካሌንደሩ በሺሕዎች በሚቆጠር ኮፒዎች ተባዝተው ሲሰራጩ የመንግሥት የደኅንነት ኀይሎቸ መቆጣጠር እንዳልቻሉ አትቷል። በእነዚህ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ሁሉ የአንዳርጋቸው እንቅስቃሴ ነበረበት፤ ስልክ እየደወሉ ለአክቲቪስቶች የሞራል ድጋፍ ይሰጣሉ፣ ይመክራሉ፤ ገንዘብ ይልካሉ። በሌላ በኩል በተለይ ብአዴን ውስጥ እርሳቸው ያደራጁት እና የሚረዱት ቡድን የመንግሥት ምሥጢሮችን አሾልኮ እያወጣ ለታጋዮች ይልካል።

ሁለገብ ትግል

የሚገርመው በአገር ውስጥ የሚደረገው ሕቡዕ ሰላማዊ ትግል እያንሰራራ ሲመጣ ትግሉን በቅርብ የሚከታተሉት እና የሚያግዙት አቶ አንዳርጋቸው በእንቅስቃሴው ላይ ያላቸው እምነት እየደበዘዘ መምጣቱ ነበር። ይህ ጎልቶ መታየት የጀመረው በተለይ በብርሃኑ ነጋ መጽሐፍ የሕትመት ሂደት ወቅት ነው። በመጽሐፉ አዲቲንግ ሲተባበሩ የነበሩት አንዳርጋቸው የብርሃኑን ጽንፈኛ የሰላማዊ ትግል አቀንቃኝነት አልወደዱትም። “ኢሕአዴግ ብረት አንስቶ የሚገዳደረው ከሌለ፤ በሰላማዊ ዐመጽ ብቻ ለውጥ አይመጣም” ሲሉ ለአክቲቪስቶች በጻፉት ኢ-ሜይል ጥርጣሬያቸውን ገልጸዋል። ለብርሃኑ ራሳቸው ወደ እስር ቤት ተከታታይ ደብዳቤዎችን በመላክ ሰላማዊ ትግል የተዘጋ በር እንደኾነ ለማሳመን ሞክረዋል። ይህ አቋማቸው ኃብታሙን የመሰሉ ታጋዮችን አስኮርፏል። በውጪ አገርም ከሰላማዊ ትግል ወደ ሁለገብ ትግል መሸጋገር የሚለው የሰውየው አቋም ያልጣማቸው በርካቶች ነበሩ፤ የቅርብ አጋሮቻቸውን ጨምሮ። እርሳቸው ግን ልክ ከምርጫው በፊት “ኢህአዴግ በምርጫ ሥልጣን አይለቅም እንደሚለው አቋማቸው አሁንም ሐሳባቸውን ሳያወላለውሉ መግፋት ጀመሩ። በተለይ ለብርሃኑ ነጋ የሚልኩት ደብዳቤ እና መልዕክት ጨመረ። ብርሃኑን ማሳመን ከቻሉ የሂደቱን አቅጣጫ መለወጥ እንደሚችሉ አላጡትም። ጎን ለጎን ከ1970ዎቹ ጀምሮ የሚያውቋቸውን አንዳንድ የኤርትራ ባለሥልጣናት ስለጉዳዩ ማማከር ጀመሩ። ኤርትራን የትግሉ ማዕከል ለማድረግ ፍላጎት ነበራቸው። ለዚህ እንዲረዳቸው ለኻያ አምስት ዓመታት አሻፈረኝ ያሉትን የብሪታንያ ዜግነት የማግኘት መብትን እያንገራገሩ ተቀበሉ እና የዩናይትድ ኪንግደም ፓስፖርት አግኝተው ወደ ኤርትራ መመላለስ ጀመሩ።

ብርሃኑ ነጋ በመጀመርያ በአንዳርጋቸው ሐሳብ አልተስማሙ ነበር። በ1ኋላ ግን ቀስ በቀስ እየተረቱ መጡ። በ1999 ዓ.ም አጋማሽ የአንዳርጋቸውን ሐሳብ ሙሉ ለሙሉ ተቀበሉት። ይኹንና በኢትዮጵያ በሕቡዕ እንቅስቃሴ ለሚያደርጉ አክቲቪስቶች ይኼን ከማሳወቅ ተቆጠቡ። አንዳርጋቸው ሐሳባቸውን ለሚደግፍ አንድ ሕቡዕ ታጋኢ በጻፉት ኢሜይል “ሰውየው ተቀብሎታል፤ ስለዚህ መዘጋጀት አለብን፤ ከአሁን በኋላ ወደ ኋላ ማለት የለም” የሚል የተለመደ ቁርጠኝነታቸውን አስቀምጠዋል። በሌላ በኩል ቅንጅት ዓለም አቀፍ የከፈተውን ዌብሳይት ከአዲስ አበባ ለሚያስተዳድረው ኤዲተር ሰላማዊ ትግል ብቻ የሚል አቋም እንዳያንጸባርቅ በትኀትና ጠይቀውታል። የዌብሳይቱ ኤዲተር የአንዳርጋቸውን የኹለገብ ትግል ሥልት በተመከለከተ ተባራሪ ወሬ ሰምቶ ስለነበር በኢሜል ምላሹ በተለይ ከኤርትራ ጋር ሊፈጥሩት ስላሉት ግንኙነት ጠይቋቸው ነበር። “ሁለታችንም የራሳችን የግል ፍላጎት አለን፤ የጋራ ፍላጎትም አለን፤ ስለዚህ እየመረጥን ልንተባበር እንችላለን። የዘላለም ጠላት የሚባል ነገር የለም” ሲሉ መልሰውለታል። በሌላ በኩል የኤርትራ መንግሥት ጨቋኝ እና የራሱን ሕዝቦች ረጋጭ ኾኖ ሳለ ለዴሞክራሲ የምንታገል ኢትዮጵያውያን እንዴት ከዚህ መንግሥት ጋራ እንሰራለን በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ‘ከኤርትራ መንግሥት ጋራ መሥራት የኤርትራ ተጨቋኞችን የበለጠ መከራ ውስጥ አይከትም፤ አለመሥራትም ነጻ አያወጣቸውም። ነገር ግን የኢትዮጵያ ተጨቋኞችን ነጻ ሊያወጣ ይችላል። ትርፍ እንጂ ኪሳራ የለውም።” የሚል ቀዝቃዛ ስሌት የተሞላበት መልስ ሰጥተውታል። የብርሃኑ ነጋ የሁለገብ ትግል ደጋፊ መኾን ጭምጭምታ ሲሰማ አንዳንድ ታጋዮችን ተስፋ አስቆረጠ። ሌሎች ግን “አማራጭ የለም” ሲሉ ተቀበሉት። “ምንግሥትን ይቅርታ ብዬ ከእስር ቤት አልወጣም” ሲሉ የነበሩት ፕሮፌሰር ብርሃኑ በየትኛውም መንገድ ከእስር ቤት መውጣት እንዳለባቸው ወሰኑ። “እኔና ጥቂት ታሳሪዎች የይቅርታ ፊርማ የሚለውን አማራጭ የተቀበልነው እነዚህን ሰዎች አደብ ለማስገዛት ብቸኛው አማራጭ የኀይል እና የዐመጻ መንገድ መኾኑን ተገንዝበን ነው” ይላሉ ፕሮፌሰር ብርሃኑ።

ፕሮፌሰሩ ከእስር ቤት ከወጡ ከጥቂት ወራት በኋላ በአሜሪካ ለቅንጅት ደጋፊዎች ባሰሙት የ28 ገጽ ንግግር ይህ አቋማቸውን ማሳየት ጀመሩ። ከዚያ በፊት ከአንዳርጋቸው ጋር ለንደን ላይ ተገናኝተው ለአንድ ሳምንት ያህል በስትራቴጂ እና ታክቲክ ጉዳይ ተወያይተዋል። አቶ አንዳርጋቸው ከኤርትራ ጋራ ስለደረሱበት ሥምምነት ገለጻ አድርገውላቸዋል። “ለግንቦት ሰባት ንቅናቄ መሠረት የጣልነው ይኼኔ ነው” ይላሉ ብርሃኑ። እነዚህን ዝርዝር ነገሮች የኢሕአዴግ ደኅንነት ሙሉ ለሙሉ ባያውቅም የአንዳርጋቸውን የተሳትፎ ደረጃ ግን በሚገባ ተረድቶታል። በጥር ወር 1998 እና ከዚያ በኋላ የተያዙ ሕቡዕ ታጋዮች በሙሉ ከቶርቸር በኋላ በመጀመርያ የሚጠየቁት ጥያቄ “ከአንዳርጋቸው ጋራ ያለህ ግንኙነት ምንድን ነው?” የሚል ነበር። ከምርጫ 97 በፊት ግንባሩን ስጋት ላይ ጥለውት የነበሩት አንዳርጋቸው አሁን የመንግሥቱ ዋነኛ ጠላት ኾነው ወጡ።

መፈንቅለ መንግሥት

ነገር ግን እስከ ሚያዚያ 2001 ዓ.ም ድረስ አንዳርጋቸው ኢሕአዴግ ላይ የደቀኑት አደጋ “የሞት እና ሕይወት” (ኤግዚስቴንሺያል ትሬት) አልነበረም። በዚያ ወር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት “በግንቦት ሰባት የተቀነባበረ መፈንቅለ መንግሥት አከሸፍኩ” ሲል ገለጸ። በኢትዮጵያ መንግሥት ዘንድ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው አቀነባባሪ ተብለው የታመኑት አቶ አንዳርጋቸው ነበሩ። ትልቁ ጥያቄም “ አንዳርጋቸው በተለይ በሚሊታሪ ውስጥ የዘረጉት መረብ ምን ያህል ሰፊ ነው?” የሚል ነው። ከዚያ በኋላ በመንግሥት ደኅንነት የተደረጉ ምርመራዎች የሰውየው መረብ መዘርጋት የተጀመረው ከ1998 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ ሊኾን እንደሚችል አሳየ። ይህ ባለሥልጣናቱን አስደነገጠ። ከአንዳርጋቸው ጋራ ግንኙነት ሊኖራቸው ይችላሉ የተባሉ መኮንኖች በመላምት ሳይቀር ተጠርጠረው ተለቃቅመው ታሠሩ፤ ወይም ከሥራ ተባረው ጥብቅ ቁጥጥር ተደረገባቸው። መንግሥት በእርሳቸው ላይ የሚያደርገውን ክትትል አጠናከረ።

ከመፈንቅለ መንግውቱ ሙከራ መክሸፍ እና አንዳርጋቸው በሚሊታሪ ውስጥ የገነቡት መረብ መበጣጠስ በኋላ የነበሩ ጥቂት ዓመታት ለግንቦት ሰባት አስቸጋሪ ጊዜያት ነበሩ። የተለያዩ እንቅስቃሴዎች አለመሳካት አንዳንዶች ድርጅቱን በፕሮፖጋንዳ እና ገንዘብ በመሰብሰብ ብቻ የሚኖር “አስትሮተርፍ ቡድን” ብለው እንዲሰይሙት አደረገ። የኤርትራ መንግውት ትግሉ ፈቀቅ እንዲል አይፈልግም የሚሉ የቀድሞ የግንቦት ሰባት አባላት እና ሌሎች የአሥመራ ተሞክሮ ያላቸው ታጋዮች በሚዲያ እየወጡ የድርጅቱን አካሄድ መተቸታቸውን አጧጧፉ። በተለይ ዋነኛ አደራጁ አንዳርጋቸው “ከፋፋይ፣ የማይሰማ፣ የኢሳያስ አሻንጉሊት” ተባሉ። ከሁለት ዓመታት በፊት ለንደን ላይ ያገኛቸው የቀድሞ የግንቦት ሰባት አባል ስለ ቡድኑ ክስረት ሲጠይቃቸው የአንዳርጋቸው መልስ አጭር ነበር፤ “ድል ሁሉንም መልሶ ይሰበስባል”። ልክ በምርጫ ወቅት እንዳሳዩት ጠባይ ኹሉ አንዳርጋቸው ይህን እንቅስቃሴያቸውን ይዘው አለቅም አሉ። በዚህ መጥፎ ጊዜ ወደ አሥመራ መመላለሳቸውን እና ለማደራጀት መሞከራቸውን አጠናከሩ እንጂ አልቀነሱም። እንዲያውም አንድ የግንቦት ሰባት አባል “ አንዳርጋቸው ወደ ኤርትራ ይመላለሳል ሊባል አይችልም፤ እዚያው ይኖራል እንጂ” ብለዋል። ፕሮፌሰር ብርሃኑ “የፖለቲካ፣ የማደራጀት፣ የጽሕፈት ሥራዎችን ኹሉ በኤርትራ የሚመራው እርሱ ነበር በዚያ ያለን የሙሉ ጊዜ እና የሙሉ ሥልጣን እንደራሴ እና አምባሳደር አንዳርጋቸው ነበር። ጉዳይ ሲኖረው ብቻ ከከተተበት ይወጣል።” ይላሉ። ለኢሕአዴግ የአንዳርጋቸው ያለመታከት እና ያለማሰለስ ራስ ምታት ነበር። እርሳቸውን ማስወገድ ከቻሉ ግንቦት ሰባትን እንደሚፈረካክሱት ጽኑ እምነት ነበራቸው። ደኅንነቱ አቶ አንዳርጋቸው ስኀተት ሲሠሩ ጠብቆ ተወርውሮ ለማጥቃት አደባ።

ሰኔ 11 ቀን 2006 ዓ.ም፦ አንዳርጋቸው የግንቦት ሰባት ሥራ ለማካሄድ ዱባይ ገቡ። እንደተለመደው ዱባይ ያሉ የኢትዮጵያ መንግሥት ዐይኖች እግር በእግር ይከታተላሉ።፡በዱባይ አራት ቀን ቆይተው እሁድ ሰኔ 15 ቀን በኤርትራ አየር መንገድ ወደ አሥመራ ለመብረር መቀመጫ ተይዞላቸዋል። ይኹንና ለትግል አጋሮቻቸው ደውለው ‘ምናልባት ሥራው በሰዓቱ ሊጠናቀቅ እንደማይችል እና ባሰቡት ጊዜ መብረር ካልቻሉ ሁለት ቀን ቆይተው ማክሰኞ ዕለት በኤርትራ አየር መንገድ ወደ አሥመራ እንደሚሄዱ ገለጡላቸው። እሁድ አመሻሽ ላይ ሥራቸውን ቢያጠናቅቁም በረራው ላይ አልደረሱበትም፤ ነገር ግን ሁለት ቀን ዱባይ መቆየት ስላልፈለጉ ሌሎች ወደ አሥመራ የሚጓዙ ዐየር መንገዶችን ማፈላለግ ጀመሩ። ከዱባይ ተነስቶ በሰንዐ አድርጎ ኤርትራ የሚገባ የየመን ዐየር መንገድ በረራም አገኙ። ሳያመነቱ ትኬቱን ቆረጡ። የኢትዮጵያ መንግሥት በትዕግሥት ግን ያለ ብዙ ተስፋ ሲጠብቀው የነበረውን ስኀተት ሠሩ።

አንዳርጋቸው ደኅንነታቸውን በመጠበቅ በኩል ያላቸው አቋም አጋሮቻቸውን ሳይቀር የሚያደናግር ነው። አንዳንድ ጊዜ የሚከተሉት የጥንቃቄ ሥነ ሥርዐት እጅግ የተዘረዘረ ነው። ሌላ ጊዜ ደግሞ ቸልተኝነት ይታይባቸዋል። ለምሳሌ ከምርጫ 97 በፊት ኢሕአዴግ እየተከታተላቸው እንደኾነ ሲነገራቸው ለማስጠንቀቂያዎች ትኩረት ሳይሰጡ የሰኔ አንድ ሰለባ ኾነዋል። በአሥመራ ሲንቀሳቀሱም አንዳንድ ጊዜ ለጥቃት በሚያጋልጣቸው ኹኔታ ይዘዋወሩ እንደነበር ጉዳዩን የታዘቡ የግንቦት ሰባት ታጋዮች ይገልጻሉ። በሌላ በኩል ፕሮፌሰር ብርሃኑ እንደሚሉት ከግንቦት ሰባት አባላት ኹሉ በላይ የደኅንነት አደጋን በመመዘን እና በመመተር እርሳቸውን የሚያህል የለም። የየመኑ ጉዞ የዚህ ተቃርኖ ውጤት ነው። ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ የመን በፖለቲካ ቀውስ የተዘፈቀች፣ ያልተረጋጋች አገር ነች። መንግሥቷ ደካማ ነው። የተለያዩ የጦር አበጋዞች እና ኹከታዊ ቡድኖች የአገሪቱን ቦታዎች ሸንሽነው ያለ ጣልቃ ገብነት ያስተዳድራሉ። የአገሪቱ የደኅንነት ኃይሎች መጠነ ሰፊ መረብ ዘርግተው ገንዘብ እየተቀበሉ በርካታ ወንጀሎችን ይፈጽማሉ። ለኢትዮጵያ መንግሥት አንዳርጋቸውን ለመያዝ ከዚህ የተሻለ አጋጣሚ አልነበረም። አቶ አንዳርጋቸው ከዚያ በፊት በተደጋጋሚ በሰንዐ በኩል ወደ አሥመራ መሻገራቸው ይህን የደኅንነት አደጋ ችላ እንዲሉና እንዲዘናጉ አድርጓቸዋል። ሰኞ ጠዋት ከዱባይ ወደ ሰንዐ አመሩ። ለኢሕአዴግ ክፉኛ ራስ ምታት እና ዋነኛ ጠላት የነበሩ ታጋይ ተገቢ ከለላ ሳያበጁ ግንባሩ ወጥመድ ውስጥ ሰተት ብለው ገቡ።

You may also like...