cultural-attraction-stunning-13

አርከበ ዕቁባይ እና ፖስት መለሲዝም

cultural-attraction-stunning-13

By Sebat Kilo

(ሜሮን አ.)

ታስታውሱ እንደኾን በኢትዮጵያ ጉዳይ በዊኪሊክስ በኩል ከሾለኩ መረጃዎች መካከል ከፍተኛ ክብደት ተሰጥቶት የነበረው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካሪ የነበሩት ፓትሪክ ጊልኪስ የዶክተር አርከበ ዕቁባይን እና የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን የሥልጣን ፉክክር አስመልክቶ ለአሜሪካ ኤምባሲ ያስተላለፉት መረጃ ነበር። እንደ ፓትሪክ ጊልኪስ በ2000 ዓ.ም የክረምት ወራት በተደረገው የሕወሓት ኮንግረስ ለፓርቲው ሊቀ መንበርነት ምርጫ አቶ መለስ በዶክተር አርከበ ተሸንፈው ነበር። ያኔ አርከበ “አቶ” ነበሩ።

በርግጥ ብሪታንያዊው ፓትሪክ ጊልኪስ የአገራቸው ሰዎች ‘አፈ ደማቅነት’ በሚሉት ባሕርይ ይታወቃሉ። ጋዜጠኛ በነበሩበት ጊዜ ሳይቀር ነገር ማጋነን፣ በሚጽፉት ጽሑፍ ውስጥ ከመሬት የተሰበሰቡ መረጃዎችን ብቻ ሳይኾን ከአዕምሮ የተወለዱ ቅመማ ቅመሞችን መጨመር ይወዱ ነበር። እውነትን ታጥፋ እስክትሰበር ሊጫወትባት የተዘጋጀ የቀድሞ ጋዜጠኛ ለኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥሩ የኮሚዩኒኬሽን አማካሪ መኾን ቢችልም የሚያሾልከውን መረጃ ለማመን ግን ይከብዳል። ይኹንና የጊልኪስን “ዝና” የሚያውቁ ሰዎች ሳይቀሩ ይኼን ዜና ሙሉ ለሙሉ ባይቀበሉትም “እሳት ከሌለ ጭስ የለም” ሲሉ ትኩረት ሰጥውት ነበር። ዶ/ር አርከበ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ የነበራቸው የእርስ በእርስ መደባበር የከተማ ተረት ተረት ኾኖ ቆይቷል፤ እሳቱ እርሱ፤ ጭሱ የሕውሓት ኮንግረስ።

በአዲስ አበባ ከንቲባነት ባሳዩት ብቃት በከተማዋ ልኂቃን ዘንድ ሞገስ አግኝተው የነበሩት አርከበ ከምርጫ 97 በኋላ የሥራ እና ከተማ ልማት ሚኒስትር ደዔታ ኾነው ሲያገልግሉ ቆዩ። ይህ በአደባባይ ያላቸውን ፖርተፎሊዮ ቀነሰው። ነገር ግን በሕወሓት እና ኢሕአዴግ ውስጥ የከባድ ሚዛን ተጫዋችነታቸው ቀጠለ። በተለይ በምሑራዊ አቅማቸው ራሳቸውን ከመለስ አሳንሰው የማይመለከቱ፣ በመለስ ዙሪያ የተገነባ የነበረውን ባዕደ አምልኮ የማይወዱ እና መለስ የሚያመነጯቸውን የፖሊሲ ሐሳቦች ከመንቀፍ እና ከማብጠልጠል የማይመለሱ እንደነበር ይነገራል።

በአስረኛው የሕወሓት ኮንግረስ የመተካካት ፍልስፍና ተጠቅሶባቸው ከሥራ አስፈጻሚ ኮሜቴ አባልነት ሲገለሉ በደስታ አልተቀበሉትም፤ የመለስ ተንኮል አድርገው እንጂ። ነገር ግን ይህ ኣጋጣሚ ምሑራዊ አቅማቸውን የበለጠ እንዲያሳድጉ እና የትንተና ክኀሎታቸውን እንዲሞርዱ ፋታ ሰጣቸው። በዩኒቨርስቲ ኦፍ ለንደን ስኩል ኦፍ ኦሪየንታል ኤንድ አፍሪካን ስተዲስ (ሶአስ )ዶክትሬት ተማሪነት ተመዝግበው በኢንደስትሪያል ኢኮኖሚክስ ተመረቁ። የመመረቂያ ጽሑፋቸውን የጻፉትም በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪያል ፖሊሲ ላይ ነው። የአቶ መለስ ሞትም የአርከበን ምሑራዊ ሥፍራ በንጽጽር አሳደገው። ኢሕአዴግ እሳት የላሱ ኮሌጅ የበጠሱ አባላት አሉት። ነገር ግን ከግዙፍ ጎምቱዎቹ መካከል ዶክተራል ዲዘርቴሽን የጻፉት ኢምንት ናቸው።

አቶ አርከበ ባለፉት ኹለት ዓመታት የፖስት መለሲዝም ሐሳብ መሪ ኾነው ብቅ እንዳሉ የእረኛ ወሬ ኾኗል። ፖስት መለሲዝም የኢሕአዴግ ፍልስፍና ከመለስ የተሻገረ እና መሻገር ያለበት እንደኾነ የሚያምን ነው። አቶ አርከበ የዚህ ሐሳብ አቀንቃኝ መኾናቸው አይገርምም። የዶክትሬት መመረቂያ ጽሑፋቸውን የተመለከተ አቶ አርከበ ብዙ የድርጅቱ ካድሬዎች ከሚያምኑት እና የመንግሥት ፕሮፖጋንዳ ከሚያትተው በተቃራኒ ኢሕአዴግ “ስኬታማ” ፖሊሲዎቹ ላይ የደረሰው ባንድ ሰው ምትሐታዊ የማሰብ ብቃት ላይ ተመርኩዞ ሳይኾን ከሥራ በመማር (learning-by-doing) እና የጋራ ብልኀት (collective wisdom) አማካኝነት መኾኑን እንደሚያምኑበት ይረዳል።

የኢኮኖሚ ቲዎሪ ታሪክን በዝርዝር የሚያውቅ በእነዚህ ሐሳቦች መካከል ያለውን ልዩነት አያጣውም። ልዩነታቸውን ለማወቅ ታላቁ ኢኮኖሚስት ኬኔት አሮው የተጠቀሙትን አንድ ምሳሌ መመውሰድ ጥሩ ነው። ብስክሌት መጋለብ ስንለማመድ በኢንጂነር የተጻፈ ማኑዋል አንሸመድድም፤ ብስክሌቱ ላይ ቁጭ ብለን እየነዳን፣ እየወደቅን፣ እየተነሳን እንማራለን እንጂ። ማኑዋሉን እንደ ጠበቃ ቃል በቃል ብናጠናው እና ብንሰነጣጥቀው የብስክሌት መጋለብ ኤክስፐርት አንኾንም። ይህ በልምድ ተፈልጎ የሚገኝ ድብቅ እውቀት (tacit knowledge) ነው። በተቃራኒው የአውሮፕላን አብራሪ ለመኾን ማኑዋሎችን መብላት እና መጠጣት አማራጭ የለውም። ብስክሌትን ለመንዳት መነሻ መሠረታዊ እውቀት አያስፈልግም፤ ወይም የተዋጣለት የአውሮፕላን አብራሪ ለመኾን ልምድ አያስፈልግም ማለት አይደለም። ምሳሌው የሚነግረን፦ የትኛው ዐይነት እውቀት ለየትኛው ዐይነት ተግባር የበለጠ እንደሚያስፈልገን ነው። ኢሕአዴግ ስለ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፕሮፖጋንዳ ሲያቀርብ ወይም ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ስለዚያው ሲዘግቡ ብዙ ጊዜ የስኬቱ ምንጭ ተደርገው የሚታዩት አቶ መለስ የተባሉ ማዕከላዊ ችግር ፈቺ (central problem-solver) ናቸው። አቶ አርከበ መጽሐፍ ኾኖ በወጣው የመመረቂያ ጽሑፋቸው ግን ቴክኒካል ቃላትን እየተጠቀሙ በውስጠ ዘ “ኧረ ወዴት ወዴት፣ ኧረ ወዴት ወዴት” ይላሉ።

ፖስት መለሲዝም ከእንደዚህ ዐይነት “ታላቁ መሪ፣ ኹሉን አድራጊ፣ ኹሉን ፈጣሪ” ተረት ተረት እናምልጥ የሚል ነው። ከግለሰቦች “ጂኒየስነት” ይልቅ ለሙከራ እና ወድቆ ለመነሳት ብልጫ ይሰጣል። “መለስ ምን አስበው ይዀን” እያሉ የእርሳቸውን ዐጽም ከመጠየቅ ለአሁን እና ለእዚህ የሚኾኑ ሙከራዎችን እየዘየድን እና እየተማርን እንሒድ ይላል። ነገር ግን የአርከበን መጽሐፍ ሲያነቡ ሰውየው ስለወደፊቱ ጥርጣሬ ሲታይባቸው እና ብዙ የማናውቃቸው እና በተሞክሮ የምንማራቸው ነገሮች እንዳሉ ሲያስቡ የሚያሳይ መረጃ አያገኙም። ይልቁንስ ወደፊት የምንሔድበትን አቅጣጫ በዝርዝር የሚያውቁ፣ የምንደርስበትን ቦታ ያለማመንታት የሚናገሩ ሰው ይመለከታሉ።

ይኸን ካደረግን ይኼ ይኾናል፣ ያውም ከ15 ዓመት በኋላ ብለው ያለ አንዳች ማቅማማት ይተነትናሉ። በሠርቶ መማር ፍልስፍና የሚያምን ቀንደኛ መመርያው የእውቀት ትኀትና (epistemic humility) ነው። ዶ/ር አርከበ ይኼን ትኀትና የሚያሳዩት ስላለፈው፣ ስለ ታሪክ ሲተርኩ እንጂ፤ ስለ ወደፊቱ ሲተነብዩ አይደለም። ይኽ ደግሞ “ስለ ሙከራ የሚያወሩት የመለስን ሞገስ ለመቀነስ እንጂ እውን ከምር አምነውበት ነው?” ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል። ኧርቪንግ ክሪስቶል ስለ ምሑራን ሲጽፉ “ቀድሞ ያሰቡትን በመጽሐፍ ጥቅስ የሚያስደግፉ” ይሏቸዋል። ዶ/ር አርከበ ከሶአስ የእውነተኛ ምሑርነት ካባ ተጎናጽፈው ወጥተዋል።

You may also like...