Consectetur adipisicing elit, sed do eiusmod tempor incididunt ut labore et dolore magna aliqua. Ut enim ad minim veniam, quis nostrud exercitation ullamco laboris nisi ut aliquip ex ea commodo.

ሁሉም ጊዜው ሲደርስ ይፃፋል!

Consectetur adipisicing elit, sed do eiusmod tempor incididunt ut labore et dolore magna aliqua. Ut enim ad minim veniam, quis nostrud exercitation ullamco laboris nisi ut aliquip ex ea commodo.

አብርሃ በላይ

የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ያበቃበት ወቅት ነው። አንዳንድ ፈራ ተባ እያሉ መለስ ዜናዊን ሲወቅሱ የነበሩ ከፍተኛ የህወሓት አመራር አባላት የተባረሩበት ሰዓት ነው። የዛሬን አያድርገውና፤ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት፤ አይደለም በሀገር ውስጥ፤ በዳያስፖራ የምንኖር ኢትዮጵያውያን ሁሉ አስጨንቆ፤ አቀራርቦን ነበር። ታድያ በዚህ ሁኔታ ላይ እያለን፤ አንድ ወዳጄ ነገ ቅዳሜ ወደ ፖርትላንድ ሄደን ለምን ጊዜያችንን አናሳልፍም አለኝ። ፖርትላንድ
የኦሬገን ስቴት ዋናና ትልቅዋ ከተማ ናት። “ፖርትላንድ ምን ተገኘ?” ብዬ ጠየኩት። አንድ ወዳጃችን አዲስ ሬስቶራንት ስለሚያስመርቅ ሁላችንንም ጋብዞናል። በዛ ብለን ስለምንጓዝ ጉዞውን ትወደዋለህ። እና አብረኸን እንሂድ ብሎ ጠይቆኝ፤ ጉዞው በማግስቱ ሆኖ፤ በአንድ መኪና አራት የምንሆን ጓደኞች ወደ ፖርትላንድ አመራን።

የበጋ ወር ስለሆነ፤ የማለዳ ፀሀይ ፏ ብላ ውጥታለች፤ የአበሻ ሳቅና ጨዋታ ከአገሩ ተፈጥሮና ከአገርኛ ሙዚቃ ጋር ተቀላቅሎ ልብ በደስታ ይሞላል። ሦስት ሰአት ያህል እንደተጓዝን ፖርትላንድ ገባን። በቀጥታ ወደ ሬስቶራንት አስመራቂው መኖሪያ ቤት ሄድን። የሀበሻ ምግብና መጠጥ አይደለም ቤቱን አካባቢውን አውዶታል። ቀጤማ ሳይቀር በወለሉ ላይ አልፎ አልፎ ተጎዝጉዟል። ሁሉም ነገር ደስ ይላል። ከገባን በኋላ፤ ጓዳ ውስጥ ምግብ ለማዘጋጀት ጉድጉድ እያሉ ከሚጣደፉት እናቶች በስተቀር፣ የቤቱ ዋናዋና ሰዎች ሬስቶራንቱን ለማስመረቅ በቅድሚያ ወደ ቤ/ክርስትያን እንደሄዱ ሰማን ። አብረውኝ የመጡት ጓደኞቼ ወደ ቤተ-ክርስቲያኑ እንሂድ ብለው ሲጣደፉ፤ እኔ እረፍት እንደምፈልግ ነግሪያቸው ቀረሁ።

እዚህ ቤት ውስጥ በሰባዎቹ የእድሜ ክልል ላይ የሚገኙ አንድ ኩታ የለበሱ ሽማግሌ አባት ብቻቸውን ተቀምጠዋል። በቅርብ ከኢትዮጵያ እንደመጡ ሁለመናቸው ይናገራል። አንገታቸውን በትንሽ ደፋ አርገው ብዙ የሚያስቡ ወይም የሚተክዙ መሰለኝ። ብቻዬን ከምቀመጥ አልኩና ወደ አዝውንቱ ጠጋ ብየ “ደሓን ድዮም አቦይ!” (ደህና ኖዎት አባቴ!) አልኳቸው በትግርኛ። “ደሓን’ዬ ወደይ!” (እግዚአብሄር ይመስገን፤ ደህና ነኝ ልጄ) አሉኝ።

“እንግዳ ነዎት ወይስ እዚሁ አገር ኗሪ?”

“ኧረ እንግዳ ነኝ፣ ከመጣሁ ይኸው ገና 10ኛ ቀኔ ነው።” አሉኝ።

ታድያ አገር እንዴት ነው ሰላም ነው? ብዬ ጠየኳቸው።

አይይይ! ምን ሰላም አለ ብለህ ነው ልጄ? አሉኝ፣ ደከም ባለ ድምጽ።

ደንገጥ ብዬ “ምነው? ምን ተፈጠረ?” አልኳቸው። እኚህን አባት የሳዘናቸውን ጉዳይ በጉጉት ለማወቅ ፈልጌ።

“አቶ ክንፈን ታውቀዋለህ? ክንፈ ገ/መድህን – የደህንነት ሹሙ?”

“እኮ ይኼ በቅርቡ የተገደለው?” ብዬ መለስኩ።

“አዎ! ገዳዪ ሻለቃ ፀሐዬ ወ/ስላሴኮ… ብለው ቆም አሉና … የልጄ ባለቤት ነው!” አሉ በተሰበረ ድምጽ።

“ውይ አባቴ! ያሳዝናል፤ በጣም ተጎድተዋል!” አልኳቸው፤ ሃዘኔን ለመግለፅ።

አዎ ትልቅ ሀዘን ላይ ነን። የገዳዩ ባለቤት የምወደው የታናሽ ወንድሜ ልጅ ነች። ወንድሜን በጣም ስለምወደው፤ ከልጅነትዋ እኔጋ አምጥቼ፤ ያደገችው እኔው ቤት ነው። አሁን ይኽው ከሶስት ህፃናት ልጆችዋ ጋር ከፈተኛ አደጋ ላይ ትገኛለች” አሉኝ ።

እንዴት ነው የሆነው ነገር ሁሉ የሆነው? እንዴትስ ሊገድለው ቻለ? ብዬ ጠየቅኳቸው ። ይህንኑ ጉዳይ እኔም ልጄን ስጠይቃት፣ ሻለቃ ፀሐዬ ክንፈን እንደነገ ሊገድለው፤ በዋዜማው ሚስቱን እንዲህ ብሎ አስጠንቅቋት ነበር ።

“ጠ/ሚኒስትራችን አቶ መለስ ዜናዊ በነገው እለት አንድ ግዳጅ እንድፈጽም አዘውኛል። ነገ ወደ ቤቴ ልመለስም፣ ላልመለስም እችላለሁ። ከተመለስኩ እሰዬው። ካልተመለስኩ ደግሞ፤ ባለቤቴ ጠፋ ብለሽ እንዳታስቢ። ምናልባት ጊዜው ሊረዝም ይችል ይሆናል እንጂ መመለሴ አይቀርም።
አንቺ እና ልጆቼ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ከመንግስት እንደምታገኙ ቃል ተገብቶልኛል። እቸገራለሁ ብለሽ እንዳታስቢ!” ብሎ አበራትቶ ነገሯት እንደነበር ምስጢር ብላ ለኔው እንባ በእንባ ሆና ነገረችኝ።

(በሀዘን የተነኩት ሽማግሌው አባትን ወደ ሌላ የፖለቲካ ዝርዝር ለመውሰድ ሞራሉ አልነበረኝምና
አቆምኩኝ። “ፅናቱን ይስጦት!” እያልኩ እሳቸውን ማበረታታት ያዝኩኝ።)

=====
ይህ ከላይ የገለፅኩት የፖርትላንዱ ገጠመኝ በጣም እየገረመኝ ሳለ፣ በአዲስ አበባ ከክንፈ ቤተሰብ ጋር ቅርበት ያለው ሰው ጋር ተገናኘን። ያኔ ኢትዮሚድያ የሚባል ገና አልተወለደም። ስለዚህ ስዉዬው ዘና ብሎ ነበር የሚጫወተው። የክንፈ አገዳደል ነበር ዓብይ የመነጋገሪያ ርእስ
የነበረው። እንግዳችን እንዲህ ሲል ጀመረ።

“የክንፈ እህቶች ወንድማችውን በጣም ነበር የሚወዱት። እሱም ቤተሰቡን በጣም ነበር የሚወደው፣ እህቶቹና እናቱ ከሱ ጋር አብረው ነበር የሚኖሩት። ሊገደል አከባቢ ክንፈ እንቅልፍ የሚባል ባይኑ ሳይዞር ይነጋ ስለነበር እህቶቹ በጣም ይጨነቁ ነበር። “ምነው ያለወትሮህ እንዲህ
እንቅልፍ ነሳህ?” እያሉ እህቶቹ ይጠይቁት ነበር። ብዙ ጊዜ ከነዘነዙት በኋላ “እኔ እንጃ! የምሞት፣ የምሞት ይመስለኛል!” ብሎ ለቅሶ በለቅሶ ያደርጋቸው ነበር። የፈራው አልቀረም፤ ክንፈ በአራት ጥይት ተደብድቦ ተገደለ። ቃታ ስቦ የገደለው ሻለቃ ፀሐዬ ይሁን እንጂ፣ የሞት ፍርዱ የመለስ
ቀጭን ትዕዛዝ እንደነበረች ግን የአደባባይ ምስጢር ነበር። በቀብሩ እለትም ግራና ቀኝ ተይዘው ሲያለቅሱ ከነበሩት የክንፈ እህቶች አንዷ፣ ጥቁር ካፖርት ለብሶ እሱም እያለቀሰ የነበረውን መለስ አትኩራ እያየች “ወንድሜን ገደልከው አይደል!” እያለች ትጮህ እንደነበር ቀብሩ ላይ የነበሩ ሁሉ
ያስታውሱታል። በቀብሩ ሥነስርአት ላይ ለመገኘት ጥያቄ አቅርበው የነበሩት እነ ስዬ አብርሃ በመንግስት ሚድያ በኩል በግድያው እጃቸው ሳይኖርበት አይቀርም በሚል በተነዛባቸው አሉባልታ ምክንያት ቀብሩ ላይ እንዳይገኙ ተከለከሉ።

====
ሻለቃ ፀሀዬ ክንፈን የገደለው በጊዜው አጠራር ‘ኦልድ ኤርፖርት” አከባቢ ባለ ‘የመኮንኖች ክለብ’ ግቢ ውስጥ ነበር። ወታደራዊ ዩኒፎርም ለብሶ ሰላምታ ሰጥቶ ካሳለፈው በኋላ ነበር ሻለቃው ሽጉጡን መዞ በአራት ጥይት የገደለው። በአከባቢው የነበሩ የፀጥታ ጠባቂ ኃይሎች እየጮኹ ወደ ሻለቃው ቢሩጡም፣ ሻለቃው ግን ሽጉጡን ጥሎ፤ እጆቹን ወደላይ በማድረግ ያላንዳች ግርግር እራሱን ለፀጥታ ኃይሎች ሰጥቷል። ሀኔታውን ይከታተሉ የነበሩ ሦስት የደህንነት መኪናዎች ወድያው ግቢውን ጥለው በመውጣት አንደኛዋ መኪና ወደ ቤተመንግስት በመሄድ
(መለስ እና በረከት ከጥቂት ሰዎች ጋር ስብሰባ ይመሩበት ወደነበረበት አዳራሽ ገብታ ጉዳዩን መፈጸሙ) መለስ በጆሮው እንደተነገረው፤ ሁለተኛዋ መኪና ደግሞ ወደ ክንፈ መኖሪያ ቤት ተወርውራ በመሄድ ሰዎቹ ብጣሽ ወረቀት እንኳን ሳያስቀሩ ሁሉንም አሽገው ወደ መለስ ቢሮ
መውሰደቸው፤ ሦስተኛዋ ደግሞ ወደ ክንፈ ቢሮ ሄዳ በተመሳሳይ መንገድ ሁሉም ዶክሜንቶች አሽጋ ወደ መለስ ቢሮ እንደወሰደች የደህነት ሰው ይመሰክራል።

የሚገርመው ነገር ግን ክንፈ ከጥዋቱ ሦስት ሰአት አከባቢ ተገድሎ በምሳ ሰዓት ለኢትዮጵያ ህዝብ የተነገረው የ‘ዜና’ ጉዳይ ነበር። በአጭሩ “አቶ ክንፈ ገ/መድህንን ገድሎ ሊያመልጥ የነበረው ሻለቃ ከፀጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት አግሩ ተመቶ በቁጥጥር ስር ውሏል።” ይል ነበር። ያቺ ‘ዜና’ መለስ ዜናዊ በክንፈ ግድያ እጁ እንደሌለበት ህዝቡን ለማሳመን የተነገረች የፈጠራ ሥራ ነበረች።

======
በህወሓት መሀል መከፋፈል በተፈጠረ ጊዜ፤ ክንፈ ከማን ጋር እንደሚወግን ግራ ገብቶት ነበር። ከመለስ ጋር እንዳይሆን ከኤርትራ ጋር የተደረገውን ጦርነት እንዴት በድል ዋዜማ ላይ መለስ እንዳከሸፈው፣ 70ሺ የኢትዮጵያ ወጣቶች የደም መስዋእትነት የከፈሉበትን ተግባር፤ ደመ-ከልብ እንዳደረገ፣ ሻቢያ ሙሉ በሙሉ ተደምስሶ፣ ኢትዮጵያ ቢያንስ የባህር ወደቧን እንዳታስመለስ ያደረገ ደመኛ የኢትዮጵያ ጠላት መሆኑ ወለል ብሎ ይታየዋል። ክንፈ የመለስን ጎራ ከድቶ ከነ ስዬ አብርሃ ጋር እንዳይቆም ደግሞ እነ ስዬ መለስን ከተራ ስድብ ውጪ የውሳኔ ሰዎች እንዳልሆኑ ልቡ ያውቃል።

ታድያ ክንፈም ግራ ተጋብቶ እያለ መለስ ዜናዊ ክንፈን ከጎኑ የሚያሰልፍበት ብቻ ሳይሆን ይበልጥ እነ ገብሩ አስራትን የሚያጠፋበትን ዜዴ ይዞ ቀረበ። “አንተ የደህንነት ሹም ስለሆንክ ከማንኛችንም ጋር ያልወገንክ ገለልተኛ መሆንክን አስታውቅ፤ ከእኛም ጋር ግምገማ ላይ አትቀመጥ” ይለዋል። ክንፈ ካስጨናቂው ጉዳይ ስለተገላገለ ለጊዜውም ቢሆን ደስ አለው። የክንፈ ገለልተኛ ነኝ ማለት ደግሞ ለየዋሁ የነገብሩ/ተወልደ ቡድን ትልቅ እፎይታን ሰጠ። ኃይለኛው የደህንነት ኃላፊ ገለልተኛ ነኝ ካለ መለስ አለቀለት የሚል የተሳሳተ እምነት አደረባቸው። መለስ ብቻውን ነው የቆመው፤ እንደጉም በኖ ይጠፋል ብለው በተስፋ ይጠብቁት ገቡ። ይህ ጉዳይ ሁለቱ ወገኖች በአራት ኪሎ ቤተመንግስት ተፋጠው በሰነበቱበት ጊዜ የተከሰተ እውነት ነበር። ጉዳዩ ተካርሮ፤ መለስ የካድሬዎች መንጋ ወደአዘጋጀበት ወደ መቀሌ እንዲዛወር አደረገ። ምን እንደሚፈጠር ስለማያውቅ ደግሞ ለአጭር ጊዜም ቢሆን የገለልተኛነት እፎይታን አግኝቶ የነበረውን ታማኙን ክንፈ ልዩ ኃይል ይዞ መቀሌ ብቅ እንዲል አዘዘው። ክንፈ የተባለውን ኃይል ይዞ መቀሌ ገብቶ በሚስጢር ቢከታተልም አቶ መለስ ተቀናቃኞቹን በዝረራ አሸንፎ ከጨዋታ ውጭ ሳላረጋቸው የክንፈ ገዳይ ቡድን አንዲት ጥይት ሳይተኩስ በሰላም ወደመጣበት ተመለሰ።

እነ ስዬ ከተባረሩ በኋላ የተፈጠረው ውጥረት እና የክንፈ መገደል መለስ ኋላ ላይ አሸናፊ ሆኖ ቢወጣም፣ በሀገር ክህደት የከሰሱትን ሰዎች ከሚገባቸው በላይ አግዝፎ ስላያቸው፤ እንቅልፍ ሊወስደው አልቻለም። በጦርነቱ ወቅት ዝናን ያተረፉት፤ ሆኖም ግን ከድርጅቱ የተባረሩት ሰዎች ህዝቡንና ሰራዊቱን ለአመጽ ይቀሰቅሱብኛል ብሉ ክፉኛ ሰግቷል።

በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ ትውልድ ይቅር የማይለውን ወንጀል ሆን ብሎ እንደሰራ አሳምሮ ያውቃል። ስለዚህ በዙሪያው ያሉ ሁሉ የነቁበት እና አንድ ላይ ሆነው ሊጨርሱት የተነሱ መስሎታል። ለዚህም መፍትሄ ሆኖ ያገኘው የመቀሌው የካድሬ ስብሰባ ረግጠው የወጡትን ሰዎች ሌላ አሳማኝ ምክንያት ፈጥሮ በሞት መቅጣት ነበር።ለዚህ ደግሞ ስፔሺያሊስቱ ክንፈ ገ/መድህን አዲስ ዘዴ ቀይሶ እንዲቀርብ አዘዘው። ክንፈ ግን በነገሩ ደንግጦ፤ “መለስ ምነው ምን ሆነሀል? የእነዚህ ሰዎች ጠባቂዎቻችው ሳይቀሩ አስረንባቸዋል። ቤት ንብረታችውንና መኪናዎቻቸውን
ሳይቀር ቀምተናቸዋል። እንኳን ለአመጽ ሊዘጋጁ ቀርቶ ለእለት ጉርስ የሚሆን ምግብም ተቸግረዋል። ደግሞስ እነ ገብሩ ምን እንዳይፈጥሩ ብለህ ነው እናጥፋቸው የምትለኝ?” ይለዋል።

ክንፈ የመለስን ትእዛዝ ሲቃውም የመጀመሪያው ሳይሆን አይቀርም። ዛሬ እንደማናችንም በስደት እየኖረ ያለ፤ ከመለስ ጠባቂዎች አንዱ የነበረ ሰው ምስክርነቱን ሲሰጥ እንዲህ ብሏል። “ግደልዋቸው የሚለውን ምስጢር የሰማን ጊዜ እንባ በእንባ ተራጭተን ነበር” ብሏል። ክንፈ የመግደሉ ጉዳይ “አላደርገውም” ሲል መለስ ምንም አላለም። ውስጡ ቢበግንም ፊቱ ግን ምንም አልተለወጠም። ነገሩን የተቀበለው መስሎ፤ ይህን “ብርቱ ሰው” ሳይቀድመኝ ለቅደመው ብሎ ወሰነ። “ጠርጥር፣ ገንፎም አለው ስንጥር” ይሉ የለ! በዛን ወቅት መለስ ዜናዊን ሊያጠፋ የሚችል ኃያል ሰው ቢኖር ክንፈ ገ/መድህን ብቻ ነበር። “ያቀዱትን ዓላማ በተሳካ ሁኔታ ለመተግበር ትልቁ ነገር ስሜትን መቆጣጠር መቻል ነው ሲል መለስ አንዴ በቲቪ ተደምጦ እንደነበር ሁላችንም የምናስታውሰው ነው። እውነትም ስሜቱን ተቆጣጥሮ የወደብን አገራዊ ጥቅም፤ ከተራ ፀጉር አስተካካይ ቤት ቢዝነስ ጋር እያወዳደረ በገደላት ኢትዮጵያ ላይ እያሾፈ፤ ከ20 አመት በላይ በስልጣን ላይ የኖረ ሰው ነበር።

===
ኢትዮሚድያ – Ethiomedia.com
November 16, 2015

You may also like...