የአፍሪካ ቀንድን ሥጋት ላይ ሊጥል ይችላል የተባለው የኤርትራ አዲሱ እንቅስቃሴ

ሙሐመድ ቦአዚዝ የተባለ የቱኒዚያ ወጣት በአደባባይ ራሱን በማቃጠል የለኮሰው አመፅ የዓረብ አገሮችን እንደ ሰደድ እሳት ነበር ያዳረሳቸው፡፡ ሊቢያና ግብፅ የእሳቱ ቀዳሚ ቀማሾች ይሁኑ እንጂ፣ ሳዑዲ ዓረቢያን ጨምሮ የተለያዩ የዓረብ መንግሥታት ተነቃንቀው ነበር፡፡

በወቅቱ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በሰሜን አፍሪካ የተነሳው አመፅና እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ላይ ምን ዓይነት ጫና እንደሚኖረው ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ እንዲህ ብለው ነበር፡፡

‹‹በተለያዩ የዓረብ አገሮች የተከሰተው አመፅ ከእኛ ጋር በቀጥታ የሚገናኝበት ነገር የለውም፡፡ እኛ የሚያሠጋን የመን ውስጥ ሊከሰት የሚችል ነገር ብቻ ነው፡፡ አገሪቱ ውስጥ ያለው አለመግባባት ካልተፈታና ወደ የእርስ በርስ ጦርነት የሚያመራ ከሆነ፣ የእኛ ደኅንነትና ፖለቲካ በቀጥታ የሚነካ ይሆናል፡፡ እንደ ሥጋት ሊነሳ የሚችለው ይኼ የየመን ቀውስ ብቻ ነው፤›› ነበር ያሉት፡፡ አሁን የኤርትራ ስም በአካባቢው እየተነሳ ነው፡፡ ምን ታተርፍ ይሆን?

የየመን ቀውስና የሥልጣን ሽኩቻ

ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ቢቢሲ ያስነበበው ሰፊ ትንተና፣ ‹‹የመን ውስጥ ማን ማንን እየተዋጋ ነው?›› በማለት የሚጠይቅ ነበር፡፡ የትንታኔው መነሻ እንዲህ የሚል አንድምታ አለበት፡፡

‹‹በጣም የደኸየች ነገር ግን እጅግ ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ ባላት የመን ውስጥ፣ ሥልጣን ላይ ለመቆናጠጥ የሚደረገው ትግል ለአካባቢውና ለምዕራቡ ዓለም ደኅንነት አሥጊ ነው፤›› ይላል፡፡

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ቀደም ብለው የገመቱት የእርስ በርስ ግጭት አልቀረም፡፡ በሰሜኖቹ አማፂዎችና ሥልጣን ላይ በነበረው አካል መካከል የተደረገው ጦርነት፣ የመንን ወደ ሙሉ የእርስ በርስ ጦርነት በመክተት የእልቂት አውድማ አድርጓታል፡፡

በመጠናቀቅ ላይ ባለው የአውሮፓውያን ዓመት መጀመሪያ ሁለተኛ ወር ላይ የአገሪቱ ሕጋዊ ፕሬዚዳንት አብዱላሂ ማንሱር ሃዲ ከመንበረ ሥልጣናቸውና ከአገሪቱ ዋና ከተማ ከሰንዓ ከተባረሩ ጊዜ ጀምሮ፣ ፕሬዚዳንቱን በሚደግፉና አብዛኛዎቹን የአገሪቱ ክፍሎች በቁጥጥር ሥር በዋሉት የዛይዳ ሺያ (ሴክት) ደጋፊ የሆኑት ይበልጥ ሁቲ በመባል በሚታወቁት መካከል መካከል ጦርነቱ ተፋፍሞ ቀጥሏል፡፡

የአገሪቱ የፀጥታ ኃይሎችም ቢሆኑ፣ በአንድ በኩል ቀድሞ የተባረሩትን ፕሬዚዳንት ማንሱር ሃዲ፣ በሌላ በኩል የሁቲ አማፂዎችን የሚደግፉ ተብለው ለሁለት ተከፍለዋል፡፡ እጅግ ግራ በሚያጋባ ሁኔታ የደኅንነት ኃይሉም ለሁለት በመከፈል አገሪቱን የጦር አውድማ በማድረግ ፀጥታዋ ምስቅልቅሏ ወጥቷል፡፡

የአገሪቱ ምስቅልቅል የወጣው ግን ቀደም ሲል የነበረው በሕዝቧ ድህነት ላይ በተጨመረው ጦርነት ብቻም አልነበረም፡፡ ሁለቱም ወገኖች በዓረቢያ ባህረ ሰላጤ የከተመውን የአልቃይዳ ክንፍ የሚጠሉ መሆናቸው ችግሩን የባሰ አወሳስቦታል፡፡

በዓለም አቀፍ የሽብር ወሬዎች አልቃይዳን እየቀደመ የመጣው ኢስላማክ ስቴት (ISIS) ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር በአገሪቱ ዋና ከተማ ሰንዓ አካባቢ ተከታታይ የአጥፍቶ ጠፊ የሽብር ድርጊቶች ፈጽሟል፡፡

በመቀጠልም በሳዑዲ ዓረቢያ የሚመራውና አምስት የባህረ ሰላጤው አገሮች፣ እንዲሁም ዮርዳኖስ፣ ግብፅ፣ ሞሮኮና ጎረቤት አገር ሱዳን አባል የሆኑበት የዓረብ የቅንጅት ኃይል ተፈጥሯል፡፡

ከመንበረ ሥልጣናቸው በኃይል ተነስተው ሳዑዲ ዓረቢያ በተጠለሉት ፕሬዚዳንት ሃዲ ጥሪም፣ በሰሜኖቹ የሁቲ አማፂዎቹ ላይ የአየር ጥቃት በማድረስ ቅንጅቱ የየመን ቀውስ አባብሶታል፡፡

የመን ውስጥ የተፈጠረው ቀውስ የምዕራባውያን ጥቅምና ደኅንነት የሚነካ በመሆኑ፣ በተለይ አሜሪካ ሰው አልባ ተዋጊ አውሮፕላኖች በመላክ ጥቃት ማድረሷን ቀጥላበት ነበር፡፡

ሆኖም አገሪቱን በቁጥጥሩ ሥር በማዋል ላይ የነበረው የሁቲ አማፂ ቡድን የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ሊገታው አልቻለም፡፡

በእርግጥ ከዚህም አልፎ ቢቢሲና ሌሎች የሚዲያ ተንታኞች እንደሚያስረዱት፣ የየመን ቀውስ በሺዓ በምትመራው ኢራንና በሱኒ በምትመራው ሳዑዲ ዓረቢያ መካከል የአካባቢያዊ የሥልጣን ፉክክር ገጽታም አለው፡፡ ሁለቱም ከየመን ጋር የሚዋሰኑ መሆናቸው ደግሞ ችግሩን የበለጠ አባብሶታል፡፡

የመን ቀይ ባህርን ከባህረ ሰላጤው የሚያገናኘው ባብ አልማንዳብ በመባል የሚታወቀው በዓለም እጅግ ስትራቴጂካዊ የሆነ የውኃ ሥፍራ (አብዛኞቹ የዓለም መርከቦች የሚተላለፉበት) ላይ መገኘቷ፣ ግብፅንና ሳዑዲ ዓረቢያን በትልቁ የደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው ይባላል፡፡ ከኢራን ወታደራዊና የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግላቸው የሁቲ አማፂዎች ቁጥጥር ሥር መዋሏ ደግሞ የበለጠ ያሳስባቸዋል፡፡

ይህም ብቻ ሳይሆን የአገሪቱን መንበረ ሥልጣንን በቁጥጥር ሥር አውለው፣ መንግሥትና ፓርላማ የመመሥረት ዕቅድ ቢያወጡም፣ አነስተኛ ቁጥር ካለው ከሺዓ በመምጣታቸው ሕዝባዊ ተቀባይነት አላገኙም፡፡ በደቡቦቹ የጦር አበጋዞችና የጎሳ መሪዎች እምብዛም ተቀባይነት አልተቸሩም፡፡

የኤርትራ መተንፈሻ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ተቆጣጣሪ ቡድን እ.ኤ.አ. በ2009 ባወጣው ሪፖርት የኤርትራ መንግሥት በሶማሊያ የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረትንና አልሸባብን የሚደግፉ የዓረብ አገሮች እንደ መተላለፊያ ገመድ በመሆን እያገለገለ ብቻ ሳይሆን፣ ከ2,000 በላይ ወታደሮች በማሠለፍ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚደገፈውን የሶማሊያ መንግሥት ለመጣል መንቀሳቀሱንም አረጋግጧል፡፡ በዚህም ምክንያት ተመድ የማዕቀብ ዕርምጃ መወሰዱም ይታወሳል፡፡

ድርጅቱ በኤርትራ ላይ የጣለው ማዕቀብ በጦር መሣሪያ ዝውውርና በአንዳንድ ባለሥልጣናት የመንቀሳቀስ መብት ላይ ጭምር የነበረ ሲሆን፣ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ማዕቀቡን አጠናክሮ ለሁለተኛ ጊዜ ጥሏል፡፡ የኤርትራ መንግሥት የባህሪ ለውጥ አላመጣም በማለት፡፡ የኤርትራ መንግሥት ወደ ሶማሊያ የተንቀሳቀሰበት ምክንያት በባድመ ውጊያ ያጣውን ድል መልሶ ለማግኘትና የኢትዮጵያን የበላይነት ለማዳከም ያለመ ነው ተብሎ፣ በብዙ ተንታኞች የውክልና ጦርነት ተደርጎ ነበር የታየው፡፡

የኤርትራ መንግሥት የተወሰደበትን ዕርምጃ በመቃወም በጠላት አገር ኢትዮጵያና በአሜሪካ መንግሥት ተንኮል ምክንያት ማዕቀቡ እንደተጣለባት ሲናገር ነበር፡፡

የኤርትራ መንግሥት በሚከተለው እጅግ ጨቋኝ አገዛዝ ምክንያት ከአንድ አምስተኛ በላይ ኤርትራውያን ወጣቶች ከአገር በመሸሽ ላይ ሲሆኑ፣ ወታደሩም የመዋጋት ሞራሉ እንደሌላው በተደጋጋሚ ሪፖርት ሲደረግ ተሰምቷል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ የኤርትራን ፀብ አጫሪነት በተመለከተ አልፎ አልፎ ግብረ-ምላሽ ከመስጠት ውጪ ወደ ሙሉ ጦርነት ለመግባት ፍላጎት አላሳየም፡፡ በራሱ ተዳክሞ እንዲወድቅ ነበር የተፈለገው፡፡ ለዚህም እንደ መሣሪያ ሆኖ ያገለገለው ከዓለም አቀፍ ፖለቲካ እንዲነጠል ማድረግ ነበር፡፡

በዚሁ ቀውጢ ሁኔታ ላይ የሚገኘው የኤርትራ መንግሥትና የጤና እክል የገጠማቸው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ሌላ መተንፈሻ ያገኙ ይመስላል፡፡ ሕልፈታቸው አራተኛ ዓመቱን የያዘው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ግምታቸው ትክክል እየሆነ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከየመን በምንም ሥፍራ ባትዋሰንም፣ የመን ውስጥ የሚከሰት ነገር በቀጥታ ለደኅንነቷ ሥጋት መሆኑ አሁን የተረጋገጠ ይመስላል፡፡ የአፍሪካ ቀንድም እንዲሁ፡፡

ከአሥራዎቹ ዓመታት በላይ ከዓለም ፖለቲካ የመነጠል አደጋ የገጠመው የአስመራ መንግሥት፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጀመረው እስቅስቃሴ የማተራመስ ተግባሩን በየመን ሊቀጥልበት ይችላል የሚል መረጃ እየወጣ ነው፡፡

የተባበሩት የዓረብ ኤምሬትስ የአሰብ ወደብን ለ30 ዓመታት የተከራየችው ሲሆን፣ ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር በመተባበር በአካባቢው ወታደራዊ የጦር ሠፈር ገንብተዋል እየተባለ ነው፡፡

በሶማሊያ የተመድ አጣሪ ቡድን በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት፣ ኤርትራ በየመን በመዋጋት ላይ ካሉት የዓረብ የቅንጅት ኃይሎች ጋር መተባበር ጀምራለች፡፡ የአየር ክልሏን፣ መሬቷን፣ ወደቧንና በቁጥጥሯ ሥር ያለውን የቀይ ባህር አካል የቅንጅቱ ኃይል እንዲጠቀምበት ተስማምታለች፡፡ 400 የኤርትራ ወታደሮችም ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ወታደሮች ጋር በመሆን፣ ሁቲዎችን እየተዋጉ መሆናቸውን ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል፡፡ ባለፈው ዓመት መጋቢትና ሚያዝያ ወራት ላይ ተደርሷል የተባለው ይኼው ስምምነት፣ ለኤርትራ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስገኝና የኤርትራ መንግሥት ከገባበት ማጥ ውስጥ ያዋጣል ተብሎ የሚገመት አጋጣሚ እንደሆነ ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡ ለየመን በተለይ ደግሞ ለሰሜኖቹ ሁቲዎች በቅርበት (29 ኪሎ ሜትር) ላይ የምትገኘው አገር ኤርትራ ስትሆን፣ ከኤርትራ ይልቅ ቀጥታ ተመራጭ የነበረችው ጂቡቲ ፈቃደኛ ሳትሆን በመቅረቷ ነው ይኼ አጋጣሚ የተፈጠረው፡፡

የመን ለኢትዮጵያ

‹‹በፖለቲካ ቋሚ ጠላትም ቋሚ ወዳጅም የለም›› የሚለው ብሂል የተለመደ ነው፡፡ ኤርትራ ግን በይበልጥ ያረጋገጠችው ይመስላል፡፡

ሪፖርተር በተሳተፈበት ባለፈው ዓመት በለንደን ላይ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የሽብር (ፀጥታ) ስብሰባ፣ የዚሁ የተመድ አጣሪ ቡድን አባል የሆኑት ተመራማሪ ሥጋታቸው ከሶማሊያ ይልቅ የመን ላይ እንደሆነ ተናግረው ነበር፡፡ የግምታቸው ምንጭም፣ የእርስ በርስ ጦርነቱ ካልተጠናቀቀ ኤርትራን የመሳሰሉ ሥርዓተ አልበኝነት የሚያጠቃቸው አገሮችና አሸባሪዎች መናኸሪያ ሆና እንዳትሆን የሚል ነበር ሥጋታቸው፡፡ አሁን ግምታቸው ትክክል ይመስላል፡፡

የኤርትራ መንግሥት ከኢራን ጋር መወዳጀት ጀምሮ እንደነበር፣ ሁለቱ አገሮችም ወታደራዊ ስምምነት ማድረጋቸው ባለፈው ዓመት በስፋት ሲወራ ነበር፡፡ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ በየመን የኢትዮጵያን ደኅንነትና ፀጥታ የሚከታተሉ አንድ የደኅንነት ተመራማሪ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አማፂዎችን ለዚህ ደረጃ ካደረሱ አገሮች መካከል ኤርትራ ቀዳሚ ነበረች፡፡

አሁንም ድረስ በሚስጥር የኤርትራ መንግሥት ለአማፂዎች ድጋፍ እንደሚያደርግ ይናገራሉ፡፡ የአሁኑ የተመድ ሪፖርት ይፋ ያወጣው ደግሞ የተገኘውን ጥቅም ለማጋበስ ሲባል ከዓረብ ከቅንጅት ኃይሎች ጋር በይፋ መተባበር ተፈልጓል፡፡ ‹‹ይህ ለየመንም ለተቀናጁት ኃይሎችም ምንም ፋይዳ የለውም፤›› የሚሉት የደኅንነት ተመራማሪው፣ የኤርትራ መንግሥት ይህንን ድርጊት መፈጸሙ ችግሩ ጨርሶ እንዲባባስ እንደሚያደርገው ይናገራሉ፡፡ ‹‹ሁለቱንም ወገኖች አንዱን በሚስጥር ሌላውን በይፋ እየደገፉ ችግሩን ማስቀጠል ነው፤›› በማለት፡፡

ተመራማሪው ድርጊቱ በኤርትራ ላይ የተጣለውን ማዕቀብም የሚጥስ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ወደ ኤርትራ የጦር መሣሪያ ዝውውር መፈጸሙ አይቀርም ሲሉም ያስረዳሉ፡፡ ‘‘ለዚህም የባህረ ሰላጤው የቅንጅት ኃይሎች ይህንን ጉዳይ በጥንቃቄ ሊመለከቱት ይገባል፡፡ ተመድም አስቸኳይ ተጨማሪ ዕርምጃ መውሰድ አለባት፤›› ይላሉ፡፡

ባለፈው መስከረም ወር ብቻ የቅንጅቱ ኃይሎች ሦስት የጦር አውሮፕላኖች በኤርትራ ምድር (አሰብ) መክረማቸውን ያረጋገጠው ደግሞ ሳውዝ ፍሮንት በመባል የሚታወቀው ‹‹ፎረይን ፖሊሲ ዲያሪ›› በሚባል ፕሮግራሙ የቀረበው አጭር ግን ጥልቅ መረጃ የያዘ ዘጋቢ ፊልም ነው፡፡

“Arab Coalition Expands into the Horn of Africa” በሚል ርዕስ ባሰራጨው ዘጋቢ ፊልም፣ ‹‹ይኼ ለኤርትራ ከፍተኛ የገንዘብ ምንጭ ብቻ ሳይሆን፣ እስካሁን የገጠማትን የመነጠል ችግር የሚፈታ ነው፤›› ብሎታል፡፡ በአፍሪካ ኅብረት የደረሰባትን ‹‹የሥርዓተ አልበኝነት›› ፍረጃም ነፃ ያወጣል ብሏል፡፡

‹‹በእርግጥ ኤርትራ ማንም ቢሆን ገንዘብ የሚሰጣት ከሆነ ከመደገፍ ወደኋላ አትልም፤›› ይላል በዘጋቢ ፊልሙ ላይ የቀረበው ሐተታ፡፡

ዘጋቢ ፊልሙ የዚሁ ስምምነት ዋና ዋና ዓላማዎችን የጠቀሰ ሲሆን፣ በሦስተኛና በዋናነት ግን በአካባቢው የተረጋጋችና የበላይነት ያረጋገጠችውን ኢትዮጵያን ለማተራመስ ዓላማ ይውላል ይላል፡፡

ለዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሙስሊሞች እንቅስቃሴና በአስመራ መቀመጫውን ያደረገው የአገሪቱን ተቃውሞ ኃይል ተጨማሪ የማተራመሺያ መንገድ መሆኑን ይገልጻል፡፡

በአሰብ እየተገነባ ያለው ወታደራዊ ኃይል በአፍሪካ ቀንድ ከዚህ በፊት ያልነበረና የመጀመሪያው መሆኑንም ጠቅሷል፡፡ ‹‹ለአካባቢው [ለአፍሪካ ቀንድ] አደገኛ እንቅስቃሴ›› በማለት የአፍሪካ ቀንድ የዓለም አቀፉ የግጭት እንቅስቃሴ መናኸሪያ ሊሆን እንደሚችል ግምቱን ያስቀምጣል፡፡

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሥልጣን፣ ‹‹ብዙ አገሮች በየመን ከሚገኘው የፖለቲካ ቀውስ ለማትረፍ እንደሚፈልጉ ቀድመን እናውቃለን፤›› ብለው፣ ‹‹የኤርትራ እንቅስቃሴ ግን አጠቃላይ የአካባቢውን ጂኦ ፖለቲካዊ ሁኔታ የሚቀይር በመሆኑ መንግሥት በቅርበትና በጥንቃቄ እየተከታተለ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት እያንዳንዷ ዕርምጃ እየተከታተለ ነው፡፡ በዚሁ ግርግር ትርፍ ለማግኘት የሳንቲም አኮፋዳቻውን ይዘው ይቀርባሉ፡፡ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ ቀጥተኛና የማይቀር አደጋ የሚያስከትል ከሆነ በዝምታ የሚታለፍ አይሆንም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ በየመን ጉዳይ የኢትዮጵያ አቋም ሕጋዊን ፕሬዚዳንት መደገፍ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ በመሄድ ሁለገብ ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ ባለሥልጣኑ የአሁኑ ጉዳይ በእርግጥ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት አደጋ ላይ ይጥላል የሚል ግምት የላቸውም፡፡ ‹‹ጉዳዩ ከዓረብ ቅንጅት ኃይሎች ጋር አይገናኝም፡፡ የእኛ ጉዳይ ከኤርትራ እንቅስቃሴ ጋር ብቻ በቀጥታ የተያያዘ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ሊወሰድ ስለሚቻለው ዕርምጃ በዝርዝር ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡

You may also like...